“በተሰረቀ የምርጫ ድምጽ ከዋይት ሀውስ በመውጣቴ እጸጸታለሁ”- ትራምፕ
የዘንድሮው ምርጫ ውጤት ታማኝነት የሚረጋገጠው የአሜሪካ ግዛቶች በወረቀት ድምጽ የሚሰጡ ብቻ ከሆነ ነው ሲሉ ተደምጠዋል
የሪፐብሊካኑ እጩ አሜሪካ ብቃት በሌላለው ቡድን መሪነት ውድቀት ውስጥ ትገኛለች ብለዋል
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት እና የሪፐብሊካኑ እጩ ዶናልድ ትራምፕ “በተሰረቀ የምርጫ ድምጽ ከዋይት ሀውስ በመውጣቴ እጸጸታለሁ” ብለዋል።
የአለምን ቅርጽ ይወስናል የሚባለው ከ161 ሚሊየን መራጮች በላይ የተመዘገቡበት ተጠባቂው የአሜሪካ ምርጫ ሊካሄድ በሰአታት የሚቆጠር እድሜ ቀርቶታል፡፡
በድራማ የተሞላው የዘንድሮው የምርጫ ፉክክር በምርጫ ቅስቀሳ እና በክርክር ወቅት የተለያዩ ሁነቶችን አስተናግዷል፡፡
45ተኛ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ትራምፕ በ2020ው ምርጫ መጭበርበር ዙርያ የሚሰነዝሩትን ሀሳብ አሁንም አላቆሙም ፡፡
በፔንሴልቫኒያ ከደጋፊዎቻቸው ጋር በነበራቸው የመጨረሻ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም ይህንኑ ሀሳብ አንጸባርቀዋል፡፡
ትራምፕ አሁንም የምርጫው ታማኝነት የሚረጋገጠው የአሜሪካ ግዛቶች በወረቀት ድምጽ የሚሰጡ ከሆነ እና የመራጮች ካርድ የሚጠቀሙ ብቻ ከሆነ ነው ብለዋል፡፡
“አሜሪካ ብቃት በሌለው የሞኞች ቡድን መሪነት ወደ ወደቀ ሀገርነት ተቀይራለች” ያሉት ትራምፕ አሜሪካ አሁን ለምትገኝበት ሁኔታ የዴሞክራቶች የአመራር ድክመት ተጠያቂ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም “ስልጣን እስከለቀኩበት የመጨረሻ ቀን አሜሪካ በታሪኳ ደህንነቱ የተጠበቀ ድንበር ነበራት” ሲሉ የተደመጡት ትራምፕ ካማላ ሃሪስ የሜክሲኮ ድንበርን አቋርጠው የሚመጡ ህገ ወጥ ስደተኞችን ለመከላከል የሚያስችል ብቃት የላቸውም ሲሉ ወርፈዋል፡፡
ምንም እንኳን የአሜሪካ ፍርድ ቤቶች የ2020ው ምርጫ መጭበርበሩን ማረጋገጫ ማግኝት ባለመቻላቸው ውድቅ ቢያደርጉትም ትራምፕ በምርጫው መሸነፋቸውን አምነው አያውቁም ፡፡
በዚህ የተነሳም የጃንዋሪ ስድስቱን የካፒቶል ሂል አመጽ ቀስቅሷ፤ በዚህኛው ምርጫም ትራምፕ እንደሚያሸንፉ በእርግጠኛነት መናገራቸው ተመሳሳይ ሁከት እንዳያስከትል ስጋት አንዣቧል፡፡