ትራምፕ ምርጫውን ካሸነፉ እንደሚከሳቸው ያሰፈራሯቸው እነማን ናቸው?
የዲሞክራቶች እጩ ሀሪስ ትራምፕ የዛሬውን ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ ያለገደብ ስልጣናቸውን ሊጠቀሙ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል
ትራምፕ በ2020 የተካሄደውን ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የተሸነፉት የድምጽ ስርቆት በመፈጸሙ ነው ብለው ያምናሉ
ትራምፕ ምርጫውን ካሸነፉ እንደሚከሳቸው ያሰፈራሯቸው እነማን ናቸው?
የሪፐብሊካኑ እጩ ድናልድ ትራምፕ በድጋሚ ፕሬዝደንት ከሆኑ የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን፣ የምርጫ ባለስልጣናትን እና ግራ ዘመም ፖለቲከኞችን እንደሚከሷቸው ወይም ምርመራ እንደሚከፍቱባቸው ዝተዋል።
የዲሞክራሲ ፕሬዝደንታዊ እጩ ካማላ ሀሪስ ትራምፕ የዛሬውን ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ ያለገደብ ስልጣናቸውን ሊጠቀሙ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
"ከውስጥ ያለ ጠላት"
ባለፈው ወር በምርጫው ቀን ትርምስ ይነሳል ብለው ይጠብቁ እንደሆነ በፎክስ ኒውስ የተጠየቁት ትራምፕ ትልቁ ችግር "ከውስጣችን ያለ ጠላት ነው" ሲሉ መልሰዋል።
"በውስጣችን ጤነኛ ያልሆኑ ሰዎች እና ግራ ዘመሞች አሉ... አስፈላጊ ከሆነ በብሔራዊ ዘቡ ከእዚያ ካለፈ ደግሞ በጦሩ ልክ ይገባሉ" ነበር ያሉት ትራምፕ።
በርግጥ በምርጫው እለት ብሔራዊ ጦሩን የመጥራት መብት የላቸውም። ተችዎች እንደሚሉት ከሆነ ይህ አስተያየት ትራምፕ ወደ ኃይት ሀውስ የሚመለሱ ከሆነ ጦሩን የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን ለማጥቃት ሊጠቀሙቀት እንደሚችሉ የሚጠቁም ነው።
የፖለቲካ ተቀናቃኞች
ትራምፕ በዲሞክራቷ እጩ ካማላ ሀሪስ፣ በፕሬዝደንት ጆ ባይደን፣ በቀድሞው ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ እና ትራምፕን በተቃወሙት ታዋቂ የቀድሞ የሪፐብሊካን ተወካይ በሆኑት ሊዝ ቸኒ ላይ ምርመራ እንዲከፈት ጠይቀዋል።
ትራምፕ ባለፈው መስከረም በፔንስልቬንያ በተካሄደ ሰልፍ ላይ ሀሪስ "በእድሜ ዘመናችን ለተፈጠረው ትልቅ ወንጀል" ተጠያቂ ናቸው ብለዋል። ትራምፕ ሀሪስን ተጠያቂ ያደረጉት ወደ አሜሪካ ከሚደረጉ ህገ ወጥ ስደት ጋር በተያያዘ ነው።
ትራምፕ ሀሪስ "ከስልጣን ወርዳ ለፈጸመችው ድርጊት መመርመር አለባት"ብለዋል።
የምርጫ ሰራተኞች
ትራምፕ ከሳምንት በፊት በዛሬው ምርጫ ሊያጭበረብሩ ይችላሉ ያላቸውን ሰዎች ከባድ ክስ እንደሚጠብቃቸው አስፈራርተዋል።
"ይህ ክስ የህግ ባለሙያዎችን፣ ፖለቲከኞችን፣ ለጋሾችን፣ ህገወጥ መራጮችን እና ሙሰኛ የሆኑ የምርጫ ባለስልጣናትን እንደሚያካትት እወቁ" ሲሉ ትራምፕ ትሩዝ በተባለው ማህበራዊ ሚዲያቸው ጽፈዋል።
ትራምፕ አክለውም "ተገቢ ባልሆነ ተግባር የሚንቀሳቀሱ ከዚህ በፊት በሀገራችን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ይያዛሉ፤ ይከሰሳሉ፤ ይመሰመራሉ።"
ዲሞክራቶችን እንደ አጭበርባሪ የሚያዩት ትራምፕ ቢሸነፉ የምርጫውን ውጤት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ስራ ሰርተዋል።
ምንም እንኳን ፍርድ ቤቶች፣ የግዛት መንግስታት እና የራሳቸው የቀድሞ አስተዳደር አባላት አሸንፌያለሁ ማለታቸውን ውድቅ ቢያደርጉባቸውም፣ ትራምፕ በ2020 ምርጫ የተሸነፉት በማጭበርበር እንደሆነ ያምናሉ።
ተቃዋሚ ሰልፈኞች
በመላው አሜሪካ ኮሌጆች ከፍልስጤም የድጋፍ ሰልፎች በኋላ ትራምፕ የአሜሪካን ሰንደቅ አላማ ያራከሰ አንድ አመት መታሰር እንዳለበት ለፎክስ ኒውስ ባለፈዉ ሀምሌ ወር ተናግረዋል።
"አሁን ላይ ሰዎች ህገመንግስታዊ ነው ይላሉ። እነዚህ ሰዎች ደደቦች ናቸው" ያሉት ትራምፕ የእስር ቅጣት እንዲጣል ከኮንግረሱ ጋር አንደሚሰሩ ገልጸው ነበር።
የቴክኖሎጂ ዘርፍ
ትረምፕ በቴክ ፕላትፎርማቸው አማካኝነት በምርጫው ጣልቃ ሳይገቡ አይቀሩም ያሏቸውን የሜታ ዋና ስራአስፈጻሚ ማርክ ዛከርበርግን እና ጉግልን እያስጠነቀቁ ነው።
ትራምፕ ሜታ በ2020ው ምርጫ ባይደንን የሚጎዱ ይዘቶች ተደራሽነታቸው ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጓል ሲሉ ከሰዋል። ዛከርበርግ የምርጫ መሰረተልማቶችን ለማሻሻል ያደረገውን እርዳታም ትራምፕ ተችተዋል።
ትራምፕ በቅርቡ "(ዛከርበርግን) በቅርብ እየተከታተልነው ነው፤ ህጠወጥ የሆነ ነገር ከሰራ ቀሪ ህይወቱን እስር ቤት ያሳልፋል" ሲሉም ዝተዋል።
አቃቤ ህጎች
ትራምፕ እና አጋሮቹ እንደማፈልጉት ያልሆኑላቸው እና ምርመራ ያደረጉባቸው አቃቤ ህጎች እንዲባረሩ፣ እንዲከሰሱ እና እንዲታሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ትራምፕ ባለፈው ሚያዚያ ወር ከታይም ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የአሜሪካ አቃቤ ህጎች አንድን ሰው ለመክሰስ ትዕዛዝ የማይቀበሉ ከሆነ እንደሚያባርሩ ተናግረዋል።"እንደ ሁኔታው ይወሰናል" ነበር ያሉት ትራምፕ።
ትራምፕ እንደገለጹት ምርጫውን የሚያሸንፉ ከሆነ በ2020 የምርጫ ውጤት ቅልበሳ ሙከራቸው ላይ ምርመራ የመሩትን የፌደራል አቃቤ ህግ ጃክ ስሚዝን ያባርራሉ።