በመንግስትና በህወሓት መካከል የተደረሰው ስምምነት ለኢትዮጵያ ምጣኔሀብት ያለው ተስፋ ምንድነው?
ኢትዮጵያ የማገገሚያ እቅድ እንደሚያስፈልጋት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ገልጸዋል
የሰሜኑ ጦርነት በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል
በጥቅምት 24፤ 2013 ዓ.ም የተቀሰቀሰው የሰሜኑ ጦርነት ከሰብዓዊ ቀውሱ ባሻገር በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይም ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል፡፡
ሀገሪቱ ለመሰረተ ልማትና ለሌሎች ግልጋሎቶች ማዋል የነበረባትን ሀብት ወደ ጦርነቱ ላይ ውሏል፡፡
ጦርነቱ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲስተጓጎል፣የዋጋ ግሽበት እንዲከስት፣ ኢትዮጵያ ከአጎአ የንግድ ትስስር እንድትሰረዝ፣ ብድር እንዳታገኝ እንዱዲሁም መጠነ ሰፊ ለሆነ የሀብት ውድመት ምክንያት ሆኗል፡፡
የጦርነቱ ያስከተለው ዳፋ
የምጣኔ-ሀብት ተመራማሪና መምህር አደም ፈቶ (ዶ/ር) ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት ሁለት ዓመታትን የዘለቀው ጦርነት አጠቃላይ ምጣኔ-ሀብቱ ላይ ጫና ማድረሱን ይናገራሉ፡፡
አደም ፈቶ (ዶ/ር) ከመንግስት በጀቶች አብዛኛው ለጦርነቱ መዋል እንዲሁም ከሕብረተሰቡና ከተለያዩ አካላት ሰነዶች በማሰባሰብ ለመንገድ፣ ለጤና ተቋማትና ለት/ቤት መዋል የነበረበት ሀብት ወደ ጦርነቱ ተመድቧል፤ ይህም በመሆኑ ጦርነቱ “ከፍተኛ ኪሳራ አድርሷል” ይላሉ።
“በመንግስት ምን አልባትም የበጀት ጉድለት እንዲኖር ያደረበት ሁኔታ ነው ያለው። ሌላም ማሕበራዊ ዋጋ አለው። አብዛኛው ሰው ያሰባሰበውን ገንዘብ ለሌላ ጉዳይ ማዋል ሲኖርበት ለጦርነቱ አውሏል።” ይላሉ።
የሰሜኑ ጦርነት እስከ ስድስት ወር ድረስ ነዳጅና መድኃኒትን የመሰሉ መሰረታዊ ግብዓቶች ይሸመቱበት ነበር የተባለው የውጭ ምንዛሬ ክምችት ላይም ጥላውን አጥልቷል። አደም ፈቶ (ዶ/ር) የውጭ ምንዛሬ ማሰባሰቢያ መንገዶች በመቀዛቀዛቸው ክምችቱ ከአንድ ወር በታች ወርዶ እንደነበር በማንሳት ሌላኛውን የጦርነቱን ተጽዕኖ ገልጸዋል።
በአንድ ሀገር የተረጋጋ ከባቢ ከሌለ በሀገር ውስጥ ያሉትንም ሆነ በሀገሪቱ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ የሚፈልጉ ባለሀብቶችን እንደሚያባርር ባለሞያዎች ይናገራሉ።
ሌላኛው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ክቡር ገና የጦርነቱ ዳፋ በውጭ መዋዕለ ነዋይ አፍሳሾች ላይ መታየቱንም ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
“ጦርነቱ ባለፉት ዓመታት ኢንቨስተሮች፣ የንግድ ድርጅቶች ማስፋፋት የሚፈልጉ ወይም ደግሞ አዲስ መቋቋም የሚፈልጉ፤ ሀገር ውስጥም ያሉ ከውጭም ፕሮግራሞችን እንዲገቱ አድርጓል።” ብለዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሁሉም ሰው ጓዳ የገባው የዋጋ ግሽበት በጦርነቱ ወቅት ጭማሪ አሳይቷል። እስከ 20 በመቶ የነበረው የዋጋ ግሽበት እስከ 35 በመቶ (የምግብ ብቻ 42 በመቶ) መድረሱ የጦርነቱ ጫና እንደ አንድ ምክንያት በባለሞያዎች ተነስቷል።
የሰላም ስምምነቱና የምጣኔሀብቱ ተስፋ
በመንግስትና በህውሓት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት ምጣኔ-ሀብቱን ሲደቁሱ የነበሩ ችግሮች እንዲቀረፉ በማድረግ ተስፋን አጭሯል።
የምጣኔ-ሀብት ተመራማሪው አደም ፈቶ(ዶ/ር) በወሩ መገባደጃ የተፈረመውና ከሰሞኑን ማስፈፀሚያ መንገዱ ላይ የተደረሰውና የሁለት ዓመታትን ጦርነት ይገታል የተባለው ስምምነት ለምጣኔ-ሀብቱ ጥሩ ገፅታ ይዞ ብቅ ይላል ብለው ያምናሉ። ለዚህም ትልቁ ምክንያታቸው የከተሞችና የመሰረተ-ልማቶች ውድመትና ሌሎች ጉዳቶች ማብቃት ከትኩረት ጋር ተደምሮ ይዞት የሚመጣው ተስፋ ነው።
“ከአሁን በኋላ ምጣኔ-ሀብቱ የዋጋ ንረት [ከዚህ] ከፍ እንዳይል፣ የውጭ ምንዛሬ ክምችት የማያሳስበን፣ በመንግስት የሚመደቡ ገንዘቦች ለውጤታማ ስራዎች የሚመድብበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህ ጠቅለል አድርገን ስናየው በሁለቱ አካላት የተደረሰው ስምምነት ምጣኔ-ሀብቱን በማነቃቃት፤ በማሳደግ ምንአልባትም ይጠፋ የነበረውን ሀብት በመመለስ ከፍተኛ የሆነ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።” ይላሉ።
አቶ ክቡር ገና በሀገሪቱ አለመረጋጋት ውጥናቸውን ገታ አድርገው የነበሩ ባለሀብቶች ለመመለስ የሰላም ስምምነቱ ተስፋ እንዳለው በመጥቀስ ተፈፃሚነቱ ላይ ግን አስምረዋል።
ስምምነቱ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ሲባል እንደ አሜሪካ ባሉ ሀገራትና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የተወሰዱ እርምጃዎችን ሊቀለብስ ይችላል ተብሏል፡፡ አሜሪካ ለ38 ሀገራት ከሰጠችውና አግዋ ከተሰኘው የንግድ ቀረጥ ስምምነት ኢትዮጵያን መሰረዟ አይዘነጋም።
የምጣኔ-ሀብት ባለሞያ የሆኑት ክቡር ገና የስምምነቱን ተስፋ በሁለት ከፍለው ያዩታል። ከአንድ ዓመት እስከ ሦስት ዓመት እና ከሦስት ዓመት እስከ አምስት ዓመት። በመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት ያን ያህል ምጣኔ-ሀብቱ ላይ ለውጥ ላይመጣ እንደሚችልም ይናገራሉ። እነዚህ ዓመታት የማገገሚያ ጊዜያት መሆናቸውን የሚናገሩት ክቡር ገና፤ ሰላም መስፈን እየተጠናከረ ሲመጣ የውጭ ባለሀብቶችና ተቋማት ለመግባት እምነት ያድርባቸዋል ይላሉ።
የምጣኔ-ሀብት ተመራማሪውና መምህሩ አደም (ዶ/ር) ስምምነቱ የሻከሩ ግንኙነቶችን ያድሳል ይላሉ። በሚወጥሉት ሳምንታት አጎአ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሀገራትና የገንዘብ ተቋማት ወደ መደበኛ ስምምነታቸው ይመለሳሉ ሲሉም ተስፋውን ተናግረዋል። ይህም ምጣኔ-ሀብቱ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል ባለሞያው።
ኢትዮጵያ ከደረሰባት የምጣኔ-ሀብት ውድመት እንዴት ታገግማለች?
የምጣኔ-ሀብት ተመራማሪውና መምህሩ አደም ፈቶ (ዶ/ር) የመጀመሪያው እርምጃ የሰላም ስምምነቱን ገቢራዊ ማድረግ ነው ይላሉ፤ ለዚህ ስምነት የሚሰጥ ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን በመጠቆም።
የምጣኔ ሀብት ባለሞያው ክቡር ገና በበኩላቸው፤ ከዚህ በኋላ ዋነኛው ስራ ከግጭት በኋላ ያለው መልሶ ግንባታ ነው ይላሉ። በጦርነቱ የጠፉ፣ የተጎዱ፣ የተበላሹ መሰረተ ልማቶችን መገንባት ዋነኛ ስራ ነው ብለዋል።
“ወደ ቀድሞ ቦታ መመለስ ቀላል ስራ አይደለም። ብዙ ድጋፍ ይጠይቃል። ኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ ይህን ስራ በራሷ ትሰራዋለች የሚለው ያነጋግራል።” ይላሉ።
በጦርነቱ ስራቸውን ያቆሙ ድርጅቶች የሚያስፈልጓቸውን አገልግሎቶችና ግብአቶች በማቅረብ ስራ እንዲጀምሩ መደረግ አለበት። በክልሎች መካከል የተቋረጡ (በተለይም በትግራይ፣ አማራና አፋር) ግንኙነቶችን ማስቀጠልና ከ30 በመቶ የተሻገረውን የዋጋ ግሽበት መቆጣጠር በአጭር ጊዜ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ መፈፍትሄዎች ናቸው።
መልሶ ግንባታው ብዙ ስራ የሚጠይቅ መሆኑን የሚያሰምሩት ክቡር ገና፤ ወገብን ጠበቅ ማድረግ አስፈላጊ ነው ይላሉ። እንደገና ወደ ኋላ እንዳንመለስ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል።
“ችግሩን እንደገና መልሶ ከማጥናት፣ የሚገነባውን፣ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከመተንበይ፤ ከዛም አልፎ ደግሞ እነዚህን ስራዎች በተቀናጀ ሁኔታ እንዲሰሩ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ድርጅት ማስቀመጥ በራሱ ትልቅ ስራ ይጠይቃል።” ሲሉ የሚያስፈልገውን ቀጣይ ስራ አመላክተዋል።
በረጅም ጊዜ መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ላይም ትኩረት እንዲደረግ ባለሞያዎች ወትውተዋል። የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካደረሰው የምጣኔ-ሀብት ድቀት ሀገራት ለማገገምና ለመልሶ ግንባት የነደፏቸውን እቅዶች ለአብነት የሚያነሱት አደም ፈቶ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያም ለመልሶ ግንባታ የረጅም ጊዜ ውጥኖችን ልታማትር ይገባል ባይ ናቸው።
“የተለያዩ ሀገሮች የተከተሉት ዘዴ ነበር። ለምሳሌ ማርሻል ፕላን ጀርመን ላይ፣ ሞልቶቭ ፕላን ሩሲያ ላይ [በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት]፣ ዶች ፕላን በጃፓን ነበር። እነዚህ ሀገሮች ከወደሙበት ሁኔታ እንዲመለሱ እቅድ አስፈልጓል። ይሄ በአንድ ዓመት፣ በስድስት ወር ሳይሆን በሚቀጥሉት ዓመታት መንግስት የሚያስብበት ይሆናል” ብለዋል፡፡
ሌላው መንግስት አይኑን ሊጥልበት የሚገባው ጉዳይ ተቀዛቅዞ የነበረውን ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ጉዳይ ነው ተብሏል። የተለያዩ ሀገራትና ድርጅቶች መዋዕለ-ነዋያቸውን በኢትዮጵያ እንዲያፈሱ መሳብ የቤት ስራ ነው ተብሏል።
አደም ፈቶ (ዶ/ር) እነዚህ እርምጃዎች ተደማምረው በጦርነቱ የወደሙን ሀብት መመለስ እንደሚያስችል እምነታቸውን ተናግረዋል።
የምጣኔ-ሀበት ባለሞያው ትልቁ የመንግስት የቤት ስራም አደረጃጀትና ስርዓት መዘርጋት ነው ይላሉ።
“ከተፈለገ በአጭር ጊዜ በሦስት አራት ዓመታት መቋቋም ይቻላል። እንደ መንግስት አደረጃጀት፣ እንደ የሚሰጠው አመራር፣ ስራው ላይ እንደሚሳተፉ ባለሞያዎች ጥንካሬ ይወሰናል።” ይላሉ ክቡር ገና ለመልሶ ማቋቋሙ ትኩረትና ቁርጠኝነት አስፈላጊ መሆኑን ሲናገሩ።
በቅርቡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴን ስለስምምነቱ ለዲፕሎማቶች ሲናገሩ ለመልሶ ግንባታ አንድ ትሪሊየን ብር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ነገርግን መንግስት እስካሁን በጦርነቱ የወደመውን የዋጋ ግምት እና ለመልሶ ግንባታ የሚያስፈልገውን እቅድ ይፋ አላደረገም፡፡
መንግስት የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን እና በጦርነት በተጎዱ አካባቢዎች የወደሙ መሰረተ ልማቶችን በፍጥነት እየጠገነ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በቀረቡ ጊዜ ተናገረዋል፡፡