የቲክቶክ ተጠቃሚዎች እየጨመረ ከመጣባቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያዊያን ዋነኞቹ ናቸው
ከቲክ ቶክ እንዴት ገንዘብ ማግኘት ይችላሉ?
ከሰባት ዓመት በፊት በቻይና ባይት ዳንስ በተሰኘው ኩባበንያ የተመሰረተው ቲክቶክ አሁን ላይ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ወርሃዊ ተጠቃሚዎች አሉት፡፡
በ2022 25 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ እንዳተረፈ የጠገለጸው ቲክቶክ ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም የተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል፡፡
ለብዙዎች ተመራጭ እየሆነ የመጣው ቲክቶክ ብዙ ተጠቃሚዎች ጊዜያቸውን እያሳለፉበት መሆኑን ተከትሎ የንግድ ድርጅቶችም በዚህ ትስስር ገጽ ላይ ምርቶቻቸውን እና አገልግሎቶቻቸውን ለማስተዋወቅ ምርጫቸው እያደረጉት ይገኛሉ፡፡
ብዙዎች ለመዝናኛነት እየመረጡት እና እየተጠቀሙት ቢሆንም ከዕለት ጉርሳቸው ባለፈ ቅንጡ ኑሮ የሚያኖራቸውን ገንዘብ እየሰሩበት ያሉ ሰዎችም ቀላል አይደለም፡፡
ለመሆኑ እርስዎ በቲክቶክ የሚለቀቁ መረጃዎችን ከመስማት እና መዝናናት ባለፈ እንዴት ገንዘብ መስራት እንደሚችሉ ያውቃሉ?
የመጀመሪያው ነገር እድሜዎት 18 ዓመት እና ከዛ በላይ ቀጥሎ የቲክቶክ አካውንት መክፈት ሲሆን የሚከፍቱት አካውንት ከቢዝነስ አካውንት ውጪ መሆን ይኖርበታል፡፡
በመቀጠልም የራስዎ የሆኑ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ማዘጋጀት እና ማጋራት ይጠበቅቦታል፡፡ ይህን በተከታታይ እና ወጥነት ባለው መንገድ መስራት የሚጠበቅቦት ሲሆን በእያንዳንዱ ፖስት ቢያንስ በወር አንድ ሺህ እና ከዛ በላይ የታዩ መሆን አለባቸው፡፡
በአጠቃላይ የቲክቶክ ክፍያ ወይም መኒታይዜሽን ለማግኘት 10 ሺህ ተከታዮችን ማፍራት፣ የተጫኑ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ያገኙት የድምር እይታ ብዛት 100 ሺህ እና ከዛ በላይ መሆን አለባቸው፡፡
እንዲሁም አካውንትዎ መቀመጫው አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያን እና አውስትራሊያ መሆኑን ማሳየት አለበት የተባለ ሲሆን የሀገራት ብዛት በየጊዜው ሊጨምርም ይችላል ተብሏል፡፡
የሚሰሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ጥሩ ጥራት ያላቸው፣ የየትኛውንም ግለሰብ፣ ቡድን፣ ማህበረሰብ፣ ተቋም በቀለሙ፣ በአስተሳሰቡ አልያም በሌሎች መንገዶች የማያገሉ እንዲሁም ለጉዳት የማያጋልጡ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
እርስዎ ባጋሯቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎች አማካኝነት ባገኙት እይታ መጠን የሚያገኙት ገንዘብ እንዳለ ሆኖ ቲክቶክ በተጨማሪነት የዘረጋቸው የገቢ ማስገኛ እና ብዙ ተከታይ እንዲኖርዎት የሚያደርግበት መንገዶችም አሉት፡፡
በተለይም እርስዎ መስፈርቶችን አሟልተው ገቢ ማግኘት ከጀመሩ በኋላ ጊዜዎትን በቲክቶክ ላይ አብዝተው የሚያሳልፉ ከሆነ ላይቭ ጊፍት፣ ቪዲዮ ጊፍት፣ ዳይመንድ ጊፍት እና ሌሎች አይነቶችም የገቢ ማስገኛ መንገዶች አሉ፡፡