የክብር ዶክትሬት እንዴት ይሰጣል?
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬትን “ለሚገባው” እሰጣለሁ ብሏል
ዩኒቨርስቲው ለክብር ዶክትሬት ጥብቅ መስፈርት እንደሚከተል ተናግሯል
የ2015 የትምህርት ዘመን የምረቃ ስነ-ስርዓት ያካዱ በርካታ ዩኒቨርስቲዎች የሰጧቸው የክብር ዶክትሬቶች መነጋገሪያ ሆነዋል።
- አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመቄዶንያ መስራች ቢኒያም በለጠ የክብር ዶክትሬት ሰጠ
- አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ “የሀገርን ውለታ ክደዋል”ያላቸውን የቀድሞ ተመራቂዎቹን ዲግሪ ሊነጥቅ እንደሚችል አስጠነቀቀ
ዩኒቨርስቲዎቹ ለሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች አስተዋጽኦ አድርገዋል ላሏቸው ግለሰቦች የክብር ዶክትሬቱን ሰጠን ቢሉም፤ አግባብነቱን፣ መስፈርቱንና ሂደቱን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ትችቶች ተነስተዋል።
"እገሌ ይገባዋል፤ እገሌ አይገባውም" የሚሉ ክርክሮችም ይሰማሉ።
በተለይም ተቋማቱ በገፍ ሰጡት የተባለው የክብር መገለጫ ዶክትሬት “ረከሰ” የሚሉ ድምጾች ተደጋግመው ተሰምተዋል።
አል ዐይን አማርኛ የሀገሪቱ አንጋፋ የሆነው ዩኒቨርስቲና ዘንድሮ ሁለት የክብር ዶክትሬቶችን የሰጠውን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መስፈርቱንና ሂደቱን ጠይቋል።
ዩኒቨርስቲው የክብር ዶክትሬትን “በማህበራዊ አገልግሎና ለሰው ልጆች ደህንነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት” ለሜቄዶኒያ መስራች ቢኒያም በለጠ እና በኪነ-ጥበብ ዘርፍ ላበረከቱት ግዙፍ አስተዋጽኦ ደግሞ ለአንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ሰጥቷል።
“የክብር ዶክትሬት” ከትምህርት ክፍሎች (ዲፓርትመንት) ጀምሮ ዩኒቨርስቲው ሴኔት ላይ የሚደርስ ሂደትን እንደሚከተል የሚናገረው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፤ ያመንኩበትንና የወደደድኩትን ሳይሆን ህግና ደንብን ተከትዬ ነው የምሰጠው ብሏል።
በጥቆማ የሚጀምረው ሂደቱ፤ ማንኛውም ሰው የክብር ዶክትሬት ይገባዋል ያለውን ግለሰብ ‘የመጠቆም’ መብት አለው ብሏል።
የዩኒቨርስቲው የኮሙኒኬሽን አማካሪ ውባየሁ ማሞ ጥቆማው በደብዳቤ፣ በኢሜልና በሌሎች መንገዶች ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።
ጥቆማውን የትምህርት ክፍሎች ተቀብለው በመመርመር መስፈርቶችን ያሟላል የሚለውን አጢነው ህግና ደንብ ያሟሉትን ወደ ዩኒቨርስቲው ሴኔት እንደሚልኩ ተናግረዋል።
“ማንኛውም ሰው (ማንነቱን ሳይገልጽ) መጠቆም ይችላል። የጠቆመው ሰው ማን ይሁን ማን አያስጨንቀንም። የትምህርት ክፍሎች ሰብስበው ህግና ደንቡን ጠብቀው ይሰራሉ። ዩኒቨርስቲው በዚህም መሰረት እንዲጸድቅ ለማድረግ ከትምህርት ክፍሎች በኋላ የማኔጅመንት ኮሚቴ ተሰብስቦ ለብቻ ያየዋል። ኮሚቴው ህጉን ያሟላል ብሎ ሲያምን ወደ ሴኔት ይቀርባል። ሴኔት ከ70 ሰው በላይ ነው። እንደገና ሴኔት ላይ የተጠቆመው ሰው ታሪክ ይነበባል። የሚያነቡት ፕሬዝዳንቱ ናቸው። ከዛ ድምጽ ይሰጣል” በማለት ሂደሩን አብራርተዋል።
የክብር ዶክትሬት እጩዎችን ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት “በቀጥታ” እንደይጠቁም የገለጹት አማካሪው፤ የትምህርት ክፍሎች ግን መጠቆም ይችላሉ ብለዋል።
የማኔጅመንት ኮሚቴው አባላት የማይስማሙባቸውን እጩዎች ካሉ “እንዲያዝላቸው በመጠየቅ” ተቃርኗቸውን ማስመዝገብ ይችላሉ ተብሏል።
እጩዎችን ለመምረጥ የሚያገለግለው መስፈርት ምንድን ነው ስንል ላነሳነው ጥያቄ “ውስጣዊ” መሆኑን የተናገሩት አማካሪው፤ “የአካዳሚክስ ተቋም ነው፤ ራስ ገዝ ነው። የሚሰጥበት መስፈርት አለው። ብዙ ነው፤ አንድ አይደለም፤ ከ20፣ ከ30 በላይ ህግና ደንብ አለ” በማለት በግልጽ መስፈርቱን አንድ ሁለት ብለው ከመናገር ተቆጥበዋል።
የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ መስፈርቱ ጠበቅ ያለ መሆኑን ግን የሚያነሱት የኮሙኒኬሽን አማካሪው፤ እጩዎች ጥቂት መስፈርቶች ባይሟሉ እንኳ እንደሚጣሉ ያለፉ ልምዶችን በማስታወስ ገልጸዋል።
ጠቋሚዎች የተጠቆሟቸውን ግለሰቦች መረጃ ሰንደው የሚያቀርቡም ሲሆን፤ የቀረቡ ማስረጃዎችን ዩኒቨርስቲው በራሱ መንገድ (ግለሰቦችንም በማነጋገር) እንደሚያጣራ ጠቁመዋል።
ለዘንድሮው ስነ-ስርዓት ምን ያህል እጩ ቀረቡ ለሚለው ጥያቄ፤ የኒቨርስቲው ውስጣዊ ነው በማለት፤የክብር ዶክትሬትን “ለሚገባው” እሰጣለሁ ብሏል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ላለፉት አራት ዓመታት የክብር ዶክትሬትን አልሰጠም።