"እውቅናው ይበልጥ ለመስራት የሚያተጋ፤ በቅንነት እና በታማኝነት ለማገልገል ሚያበረታታ ነው"-የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አለምአቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ለሴት አመራሮች ከህይወትና ከስራ ተሞክሯቸው ልምዳቸውን ለከተማዋ ሴት አመራሮች አካፍለዋል፤እውቅናም ተሰጥቷቸዋል፡፡
ከንቲባዋ ቀኑን ምክንያት በማድረግ ባልጠበቁት መንገድ ለተሰጣቸው እውቅና ምስጋ አቅርበዋል፡፡
እውቅናው በይበልጥ ለመስራት የሚያበረታታ ነውና ከእኛ የሚጠበቀው ትጋት፣ በቅንነት እና በታማኝነት ማገልገል ነው ያሉት ወ/ሮ አዳነች በአመራር ላይ ያለን ሴቶች ያለን ስኬት የብዙ ሴቶች ልፋት፣ ትግል እና ተጋድሎ ውጤት እንደሆነም መገንዘብ ተገቢ ነው ሲሉም ገልጸዋል ።
የአለም የሴቶች ቀን ታሪካዊ ዳራ?
በዓሉ በ19ኛው ክ/ዘመን መጀመሪያዎቹ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ይደርስባቸው የነበረውን የመብት ረገጣና ጭቆና በመቃወም የነጻነትና እኩልነት ጥያቄን አንግበው አደባባይ በመውጣት ለአመታት ባካሄዱት የትግል እንቅስቃሴ የተገኘ የድል ቀን ነው፡፡
ይህ የአመፅ እንቅስቃሴን መነሻ በማድረግ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘንድ እውቅናን ለማግኘት የበቃ በዓል መሆኑ ይታወቃል፡: የበዓሉ መነሻ በፈረንጆቹ 1908 በኒውዮርክ ከተማ ነዋሪ የሆኑ 15,000 ሴቶች የተሻሻለ የሥራ ሰዓትና የደመወዝ ክፍያን እንዲሁም የመምረጥ መብታቸው እንዲከበር አደባባይ መውጣታቸውን ተከትሎ ነበር፡፡ከአንድ ዓመት በኋላ የአሜሪካ ማኅበራዊ ፓርቲ ዕለቱን የሴቶች ብሔራዊ ቀን ተብሎ ሊተወጅ የቻለው።
በዓሉ ዓለማቀፋዊ ቅርፅን እንዲይዝ በ1910 ላይክላራ ዚክተን በተባለች ሴት አማካኝነት በዴንማርክ ዋና ከተማ ኮፐንሀገን በተካሔደው ዓለማቀፋዊ የሠራተኛ ሴቶች ኮንፍረስ ላይ ሀሳቡ የቀረበ ሲሆን ከአስራ ሰባት ሀገራት የተውጣጡ መቶ ተሳታፊ ሴቶች ሀሳቡን በደስታ ስለተቀበሉትም እንደ ኦስትርያ ዴንማርክ ጀርመንና ስዊዘርላንድ የመሳሰሉ ሀገራት በዓሉን በ1911 በማክበር ፈር ቀዳጅ ለመሆን ችለዋል።
ባለፈው የፈረንጆች 2011 ይሄው በዓል ለመቶኛ ጊዜ የተከበረ ሲሆን በዚህ ዓመት ሲታሰብ ደግሞ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ110ኛ ጊዜ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለ45 ጊዜ መሆኑ ነው።
በዚህ ዓመት ደግሞ በዓሉ በአለም አቀፍ ደረጃ " “Women in Leadership: Achieving an equal future in a COVID-19 world" እንዲሁም በኢትዮጵያ ‘ የሴቶችን መብት የሚያከብር ማህበሰብ እንገንባ!" በሚል መሪ ቃል የሚከበር ሲሆን፡ ደረጃ በዚህ መሪ ቃል ማክበር ያስፈለገበት ዋና ዓላማ የሴቶች ሁለንተናዊ መብት መከበር ህብረተሰቡን ለማስገንዘብና ተገቢው ምላሽ እንዲሰጥ ለማስቻል ያለመ ነው፡፡
መቼ ይከበራል?
ዛሬ ላይ በዓሉ በፈረንጆቹ መጋቢት በ8ኛው ቀን ይከበራል። ይሁን እንጂ ክላራ በተባለቺው ሴት አማካኝነት ሐሳቡ ሲጠነሰስ የተቀመጠለት ቋሚ ቀን አልነበረም። የሩሲያ ሴቶች በ1917 "ዳቦና ሰላም " በማለት ያነሱት የተቃውሞ እንቅስቃሴ የበለጠ ቅርፅ እንዲይዝ አድርጎታል፡፡ የሴቶች ቀን ዓለም አቀፍዊ አከባበር እንግዲህ የሴቶች ቀን በብዙ ሀገሮች ማለት ይቻላል ብሔራዊ በዓል ሲሆን በተለይ በሩሲያ ከዕለቱ ሦስት አራት ቀን ቀደም ብሎ የአበባው ገበያ ይደራል።
በቻይና ደግሞ በመንግሥት አስተዳደር በመፈቀዱ አብዛኛው ሴቶች የግማሽ ቀን ዕረፍት የሚሰጣቸው ቢሆንም በአንፃሩ ደግሞ ይህንን የማያከብሩ ቀጣሪዎችም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ወደ ጣሊያን ስንመጣ ደግሞ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አስመልክቶ ሴቶች ምሞሳ የተሰኘውን በቢጫና ሮዝ ቀለማት ያሸበረቀ አበባ በገፀ በረከትነት ያገኛሉ። ምክንያቱ በውል ባይታወቅም ይሔው ልማድ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በሮማ እንደተጀመረ ይታመናል።
በአሜሪካ ደግሞ መጋቢት ወር የሴቶች ታሪካዊ ወር ነው፤ የፕሬዝዳንቱ ቢሮም ለሴቶች ስኬትና ድል በየዓመቱ እውቅና ይሰጣል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ይሔው ዓለም አቀፋዊ በዓል ታላቅ የሚባል እምርታ ላይ ደርሷል። ለአብነት በጥቅምት ወር 2017 #እኔም [#metoo] በማለት የሴቶችን ፆታዊ ጥቃትና ትንኮሳ ለመቃወምና ለማውገዝ ሚሊዮኖች በማህበራዊ መገናኛ ገፆች ድምፃቸውን አሰምተዋል። ይሔው #እኔም እንቅስቃሴ በ2018 አድጎ አለማቀፍዊ ቅርፅ በመያዝ እንደ ህንድ ፈረንሳይና ደቡብ ኮሪያ ያሉ ሀገራት ይህንንኑ ዘመቻ ለለውጥ ተቀላቅለዋል።