ባልተቀጠሩ ሰራተኞች ስም ከ2 ሚሊየን ዶላር በላይ ያጭበረበረው የሰው ሀብት ባለሙያ
ግለሰቡ የሰዎችን ስም በደመወዝ መክፈያ ሰነድ ውስጥ በማስገባት እና በማጭበርበር በቁጥጥር ስር ውሏል

ሲያጭበረብር በነበረባቸው 8 አመታት ውስጥ 22 ሀሰተኛ ሰራተኞችን በመቅጠር ገንዘብ ሰብስቧል
የሻንጋይ ቴክኖሎጂ ኩባንያ የሰው ሃይል ስራ አስኪያጅ በደርዘን በሚቆጠሩ የውሸት ሰራተኞች ስም በርካታ መጠን ያለው ገንዘብ ሲያጭበረብር እንደነበር ተደርሶበታል፡፡
ግለሰቡ በኩባንያው ውስጥ የሌሉ ሰራተኞችን በደመወዝ መክፈያ ሰነድ ውስጥ በማስገባት እና ደሞዛቸውን በመሰብሰብ ድርጅቱን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በማጭበርበር ለእስር ተዳርጓል።
ይህ የማጭበርበር ድርጊት ሊደረስበት የቻለው በሀሰተኛ ስም ባስመዘገበው አንድ ሰራተኛ የተሳካ የሰዓት ሪከርድ ነበር፡፡
በርካታ ሰራተኞች በስራ ሰዓት በጊዜ ባለመድረስ የተለያየ ክስ እና ማስጠንቀቂ በሚደርስባቸው የሻንጋይ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ውስጥ ዣው ሰን የተባለ አንድ ሰራተኛ አንድም ቀን ከስራ ማርፈድ ጋር ተያይዞ ስሙ ተነስቶ እንደማያውቅ ሰራተኞችም ግለሰቡን ከስሙ በስተቀር በአካል አይተውት ባለማወቃቸው ባደረጉት ምርመራ የሰው ሀብት ስራ አስኪያጁን ማጭበርበር ሊደርሱበት ችለዋል፡፡
ያንግ የተባለው የሰው ሀይል ስራ አስኪያጅ በፈረንጆቹ 2014 የቴክኖሎጂ ኩባንያውን የተቀላቀለ ሲሆን በተለያዩ የስራ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ሰራተኞችን የማቀናጀት እና የማስተዳደር ሀላፊነት ነበረው፡፡
በዚህ ወቅት ነበር የሰራተኞችን የደመወዝ መክፈያ ሰነድ እና ወጪ የሚከታተል አካል እንደሌለ በቅጥርም ሆነ ሰራተኞችን በማባረር ዙሪያ ለማጭበርበር የሚያስችል ክፍተት መኖሩን የተረዳው፡፡
ቀጥሎም የተለያዩ የውሸት ሰራተኞችን ስም በማዘጋጀት የድርጅቱ አካል እንደሆኑ በማስመሰል የባንክ ሂሳቦችን በማዘጋጀት ከደመወዝ መክፈያ ጋር በማገናኘት ሁለት ሚሊየን ዶላር ገንዘብ ሲያጨበረብር ኖሯል፡፡
የሰው ሀብት ባለሙያው በሻንጋይ ቴክኖሎጂ ኩበንያ ስራ ከጀመረበት 2014 ጀምሮ እስከ 2022 ድረስ ለ8 አመታት 22 ሀሰተኛ ሰራተኞችን በመቅጠር ነው 16 ሚሊየን የን የቻይና ገንዘብ ማጭበርበር የቻለው፡፡
የተሳካ የስራ ሰዓት ባለው ዣው ሰን በተባለው ሀሰተኛ ሰራተኛ የተነሳ የተቋሙ ሰራተኞች በጀመሩት ምርመራ ወደ ፖሊስ የደረሰው ጉዳዩ በፍርድ ቤት ክርክር ሲደረግበት ቆይቶ ውሳኔ አግኝቷል፡፡
የሰው ሀብት ስራ አስኪያጁ ከድርጅቱ ካጭበረበረው 16 ሚሊየን የን ውስጥ 2.3 ሚሊየን የን መመለስ ቢችልም ከሰረቀው ገንዘብ አንጻር በቂ ባለመሆኑ ፍርድ ቤት በ10 አመት ከሁለት ወር እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡
የሚንሃንግ አውራጃ አቃቢ ህግ ሻንጋይ በቅርቡ ከድርጅት ሰራተኞች ፣ ከስራ ግዴታ ጋር ፣ በኩባንያ እና በድርጅት ሰራተኞች ጋር የተያያዙ ወንጀሎች ክስ መበራከቱን አስታውቋል፡፡