የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት የፊታችን ሰኞ ወደ ሳኡዲ እንደሚያቀኑ ተናገሩ
ዜለንስኪ የዩክሬን ልኡክ ከአሜሪካ አቻው ጋር የሶስት አመቱን ጦርነት ማስቆም በሚያስችሉ ጉዳዮች ይመክራል ብለዋል

የአውሮፓ ሀገራት በብራሰልስ ለኬቭ ድጋፍ ለማድረስ ሲስማሙ፥ ትራምፕ ግን "ዩክሬናውያን የሰላም ስምምነት ከመድረስ ውጭ አማራጭ የላቸውም" ሲሉ ተደምጠዋል
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ የፊታችን ሰኞ ወደ ሳኡዲ አረቢያ እንደሚያቀኑ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ የአውሮፓ ህብረት ትናንት በብራሰልስ አስቸኳይ ስብሰባ ሲያደርግ በሰጡት መግለጫ በሪያድ ቆይታቸው ከሳኡዲው ልኡል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ጋር እንደሚወያዩ ገልጸዋል።
"ከዚያ በኋላ የልኡክ ቡድኔ በሳኡዲ አረቢያ ቆይቶ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር ይወያያል፤ ዩክሬን ሰላም እንዲሰፍን አጥብቃ ትፈልጋለች" ብለዋል።
ዜለንስኪ ከኣአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በነጩ ቤተመንግስት ሲመክሩ ከታየው ንትርክ በኋላ ግንኙነታቸው እየተሻሻለ መምጣቱን መናገራቸውንም ፍራንስ 24 ዘግቧል።
የትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ትናንት በሰጡት መግለጫ ዜለንስኪ የሰላም ስምምነቱን እንደሚፈልጉ የሚጠቅስ ደብዳቤ ለትራምፕ ልከዋል ብለዋል።
በቀጣዩ ሳምንት በሪያድ አልያም በጂዳ የሚደረገው ድርድርም ለዘላቂ የሰላም ስምምነት በር የሚከፍት የተኩስ አቁም ስምምነት ይደረስበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም አብራርተዋል።
ዩክሬን የተኩስ አቁም ስምምነት መፈረም ሩሲያ የተቆጣጠረቻቸውን ግዛቶች የግሏ አድርጋ እንድትቀጥል ያደርጋል የሚል ስጋት አላት።
ፕሬዝዳንት ትራምፕን ጨምሮ የአሜሪካ ባለስልጣናትም ኬቭ በሞስኮ የተነጠቀችውን መሬት ዳግም የማግኘት እድሏ ጠባብ እንደሆነ ሲናገሩ ቆይተዋል።
ትራምፕ ትናንት ምሽቱ በነጩ ቤተመንግስት ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ "ዩክሬን ስምምነት መፈራረም እንደምትፈልግ አስባለሁ ምክንያቱም ምንም አማራጭ የላትም" ብለዋል።
"ሩሲያም ብትሆን እኔ በማውቀው የተለየ ምክንያት ስምምነት ትፈልጋለች፤ እርሷም አማራጭ የላትም" ሲሉም ነው የሳኡዲው የቀጣይ ሳምንት ምክክር ተስፋ ሰጪ ነገር እንደሚታይበት የጠቆሙት።
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ግንኙነትን የማደስ ፍላጎትና ለዩክሬን የሚደረግ ወታደራዊ ድጋፍ መቋረጥ አውሮፓ ለደህንነቷ አሜሪካ ላይ መተማመን እንደማትችል ማሳየቱን የሚጠቅሱ የአውሮፓ መሪዎች ከሰሞኑ ተከታታይ ምክክር እያደረጉ ይገኛሉ።
በትናንትናው እለትም ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ጭምር የተሳተፉበትን ምክክር በቤልጂየም ብራሰልስ አካሂደው ለኬቭ ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ ተስማምተዋል።
ክሬምሊን የፈረንሳይ እና ብሪታንያን ጨምሮ የአውሮፓ መሪዎች ከሰሞኑ እየሰጡት ያለውን አስተያየት ግጭት የሚያባብስ ነው በሚል ተቃውሟል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ አውሮፓውያን ወደ ዩክሬን ሰላም አስከባሪ ሃይል የሚልኩ ከሆነ በሞስኮ ላይ የእጅ አዙር ሳይሆን የቀጥታ ጦርነት እንዳወጁ እንቆጥረዋለን ማለታቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል።