ሂዩማን ራይትስ ዋች እስራኤል በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን በውሃ ጥም ገድላለች አለ
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ "እውነታው ከሂዩማን ራይትስ ዋች ቅጥፈት በተቃራኒው ነው" ብሏል
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ እስራኤል በጋዛ ፍልስጤማውያን በረሃብና በሽታዎች እንዲያልቁ እያደረገች ነው የሚል ሪፖርት ማውጣቱ ይታወሳል
አለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ዋች እስራኤል በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን በውሃ ጥም ገድላለች አለ።
እስራኤል ወደ ጋዛ ንጹህ ውሃ እንዳይገባ መከልከሏ ከዘር ማጥፋት ወንጀል የሚስተካከል መሆኑንም ጠቁሟል።
"በጋዛ ንጹሃን ፍልስጤማውያንን በጅምላ የመግደል የእስራኤል ፖሊሲ በተለያየ መንገድ ቀጥሏል፤ ይህ ድርጊት በ1948ቱ የጄኔቫ ኮንቬንሽን በዘር ጭፍጨፋ የሚመደብ ነው" ሲልም ነው ሪፖርቱ ያመላከተው።
የእስራኤል ባለስልጣናት "ፍልስጤማውያን ሊጠፉ እንደሚገባ" በተደጋጋሚ አስተያየት እንደሚሰጡና ወሳኙን ውሃ መከልከልም የዚሁ ፍላጎት ማሳኪያ መንገድ መሆኑንም በማከል።
የሂዩማን ራይትስ ዋች የመካከለኛው ምስራቅ ዳይሬክተር ላማ ፋኪህ፥ "የእስራኤል መንግስት ሆን ብሎ ፍልስጤማውያንን ውሃ በማስጠማት እየገደላቸው እንደሆነ ደርሰንበታል" ማለታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
184 ገጽ ያለው የሂዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርት የእስራኤል መንግስት ውሃ ወደ ጋዛ እንዳይገፋ ማገዱና ኤሌክትሪክ እንዲቋረጥ ማድረጉ ፍልስጤማውያንን በጅምላ የመቅጣት ፍላጎቱ ማሳያ ነው ብሏል።
የሂዩማን ራይትስ ዋችን ሪፖርት በተደጋጋሚ ውድቅ የምታደርገው እስራኤል አለማቀፍ ህግን አክብራ ከሃማስ የተሰነዘረባትን ጥቃት ለመመከት ወደ ጋዛ መግባቷን ታወሳለች።
ለዛሬው ሪፖርት ምላሽ የሰጠው የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "እውነታው ከሂዩማን ራይትስ ዋች ቅጥፈቶች በተቃራኒው ነው" ብሏል።
ሚኒስቴሩ በኤክስ ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ "እስራኤል የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ውሃ እና ምግብ እንዲገባ ሁኔታዎችን አመቻችታለች፤ ድጋፍ እንዳይገባ ሲያደናቅፍ የነበረው የሀማስ የሽብር ቡድን ነው" ሲል ክሱን ተቃውሟል።
የጋዛ የውሃ መሰረተ ልማቶች አሁንም ድረስ ስራቸውን እንዲቀጥሉ ማድረጉንና አለማቀፍ አጋሮች እስከባለፈው ሳምንት ድረስ በእስራኤል መተላለፊያዎች በኩል ወደ ሰርጡ ውሃ ማስገባታቸውን ጠቁሟል።
እስራኤል 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ቶን የሰብአዊ ድጋፍ ወደ ጋዛ እንዲገባ ማመቻቸቷን በመጥቀስም የሂዩማን ራይትስ ዋችን ሪፖርት አጣጥላለች።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሁለት ሳምንት በፊት በተመሳሳይ እስራኤል በጋዛ ፍልስጤማውያን በረሃብና በሽታዎች እንዲያልቁ እያደረገች ነው የሚል ሪፖርት ማውጣቱ ይታወሳል።
የመብት ተሟጋች ድርጅቱ ለስድስት ወራት ያካሄደውን ምርመራ ውጤት ይፋ ሲያደርግ እስራኤል በጋዛ የዘር ጭፍጨፋ ፈጽማለች ሲል ደምድሟል።
ሁለቱ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እስራኤልን በዘር ጭፍጨፋ የከሰሱት አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትራቸው ዮቭ ጋላንት ላይ የእስር ማዘዣ ካወጣ በኋላ ነው።