አባ ፍራንሲስ የጋዛ የዘር ጭፍጨፋ ክስ "በጥንቃቄ እንዲመረመር" ጠየቁ
እስራኤል በበኩሏ "በሰባት ግንባሮች የተከፈተብኝን የዘር ማጥፋት ጥቃት እየተከላከልኩ ነው" በሚል ውንጀላውን አጣጥላለች
የመንግስታቱ ድርጅት ባለፈው ሳምንት ባወጣው አዲስ ሪፖርት እስራኤል በጋዛ ረሃብን እንደጦር መሳሪያ እየተጠቀመች መሆኑን አመላክቷል
የሮማው ሊቀጻጻስ አባ ፍራንሲስ በጋዛ የዘር ጭፍጨፋ ተፈጽሟል በሚል የሚቀርቡ ክሶች "በጥንቃቄ እንዲመረመሩ" ጠይቀዋል።
አባ ፍራንሲስ በቅርቡ በሚያወጡት መጽሃፋቸው በጋዛ የዘር ጭፍጨፋ መፈጸሙን የሚያመላክቱ ሃሳቦችን ማከታታቸውን ቫቲካን ኒውስ አስነብቧል።
"ወንድምና እህቶቻቸው ምግብ አጥተው ረሃብ ባንዣበበባቸው ወቅት ከጋዛ እየወጡ ከሚገኙት በላይ የፍልስጤማውያን ሰቆቃ ያሳስበኛል" የሚሉት አባ ፍራንሲስ፥ ከዚህ ቀደም ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ከማንሳት ይልቅ ስለሰላም በመናገር ይታወቃሉ።
እስራኤልና ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርሱ፣ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲገባና ታጋቾች እንዲለቀቁ ሲወተውቱ የቆዩት የሮማው ሊቀጻጻስ ባለፈው አመት ታህሳስ ወር ላይ ሁለት ሴቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ከተገደሉ በኋላ ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው ይታወሳል።
የ87 አመቱ አዛውንት በቅርቡ ለገበያ ይውላል በተባለው መጽሃፋቸው ውስጥም እስራኤልን የሚኮንኑ በርካታ ሃሳቦችን ማካተታቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል።
በሮም ካቶሊካዊት ቤተከርስቲያን የእስራኤል አምባሳደር ያሮን ሲድማን ግን በእስራኤል ላይ የሚቀርቡ የዘር ጭፍጨፋ ክሶች ውድቅ አድርገዋል።
አምባሳደሩ የጥቅምት 7ቱን የሃማስ ጥቃት "1 ሺህ 200 እስራኤላውያን ያለቁበት የዘር ጭፍጨፋ ነው፤ እስራኤል ከዚህ ጥቃት በኋላ በሰባት ግንባሮች የተከፈቱባትን ጥቃቶች በመከላከል ላይ ተጠምዳለች" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የፍትህ ፍርድቤት (አይሲጄ) በደቡብ አፍሪካ አማካኝነት የቀረበውን የዘር ማጥፋት ክስ እየተመለከተ ነው። ፕሪቶሪያ የእስራኤል መሪዎች "በጋዛ የሚገኙ ፍልስጤማውያንን ለማጥፋት እየሰሩ ነው" ብላለች።
ፍልስጤማውያንን ሳይሆን አሸባሪውን ሃማስ እየተዋጋሁ ነው የምትለው እስራኤል ግን ክሱን በተደጋጋሚ ማጣጣሏ ይታወሳል።
የመንግስታቱ ድርጅት ልዩ አጣሪ ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት ባወጣው አዲስ ሪፖርት እስራኤል በጋዛ ረሃብን እንደጦር መሳሪያ እየተጠቀመች መሆኑንና ይህም የዘር ጭፍጨፋ መገለጫ መሆኑን አመላክቷል።
የሳኡዲው ልኡል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማንም በቅርቡ እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን የዘር ጭፍጨፋ እንድታቆም ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው።
በትናንትናው እለት ብቻ 50 ፍልስጤማውያን የተገደሉባትን ጥቃት የፈጸመችው እስራኤል ግን ከ43 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈውን ጦርነት ከማቆም ይልቅ አጠናክራ ገፍታበታለች።