ፍልስጤማውያን በረሃብና በሽታዎች "በቀስታ እና በተሰላ ሞት" እንዲያልቁ እየተደረገ ነው - አምነስቲ
የመብት ተሟጋች ድርጅቱ ለስድስት ወራት ያካሄደውን ምርመራ ውጤት ይፋ ሲያደርግ እስራኤል በጋዛ የዘር ጭፍጨፋ መፈጸሟን አመላክቷል
እስራኤል በጋዛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ለሚቀርብባት ክስ ውድቅ ታደርጋለች፤ ሃማስ ንጹሃንን እንደ ሰብአዊ ጋሻ እየተጠቀመ ነው ስትልም ትከሳለች
እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ መፈጸሟን የሚያረጋግጥ ድምዳሜ ላይ መድረሱን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገለጸ።
ተቀማጭነቱን ለንደን ያደረገው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ለስድት ወራት ያካሄደውን ምርመራ አጠናቆ ዛሬ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል።
ግኝቱ "ሰብአዊነትን በሚያጠለሹና የዘር ፍጅትን በሚቀሰቅሱ የእስራኤል መንግስት እና ወታደራዊ አመራሮች ንግግሮች" እንዲሁም የጋዛን ውድመት በሚያሳዩ የሳተላይት ምስሎችና ከጋዛ በተላለፉ ዘገባዎች ላይ የተመሰረት መሆኑን አምነስቲ ገልጿል።
ድርጅቱ እስራኤል የዘር ማጥፋትን ለመከላከል በ1948 ከወጣው የመንግስታቱ ድርጅት ኮንቬንሽን አምስት በዘር ማጥፋት ከሚያስከስሱ ጉዳዮች ሶስቱን ፈጽማለች ብሏል።
ሆን ተብሎ በጅምላ የሚፈጸም ግድያ፣ የአካል እና አዕምሮ ጉዳት ማስከተል እና ጥበቃ በሚያስፈልገው ቡድን ላይ የተቀነባበረ ውድመት ማድረስ በሚሉት ጥፋተኛ ሆና መገኘቱን ሪፖርቱ አመላክቷል።
በዚህም እስራኤል በጋዛ የዘር ጭፍጨፋ መፈጸሟን ከድምዳሜ ደርሰናል ያሉት የአምነስቲ ዋና ሃላፊ አንጌስ ካላማርድ፥ የድርጅቱ ድምዳሜ "በቀላል መረጃ የተሰመሰረተና ፖለቲካዊ አላማ" የሌለው መሆኑን አብራርተዋል።
"እስራኤል ፍልስጤማውያንን ለሰብአዊ መብትና ክብር የማይበቁ ከሰውነት ተራ ዝቅ ያሉ ቡድኖች አድርጋ የመመልከቷ ነገር ከወር ወደ ወር እየተባባሰ ነው፤ በአካል ልታጠፋቸው እንደምትፈልግም ማሳየቷን ቀጥላለች" ነው ያሉት ሃላፊዋ በዘሄግ በሰጡት መግለጫ።
እስራኤል በጋዛ ወታደራዊ ግብ እንዳላት እሙን ነው ያሉት ካላማርድ፥ ወታደራዊ ግቡ ግን የዘር ማጥፋት ፍላጎት አለመኖሩን ሊያሳይ አይችልም ሲሉ ተናግረዋል።
የፍልስጤሙ ሃማስ በጥቅምት 7 2023 በእስራኤል ላይ ባደረሰው ጥቃት ምክንያት እስራኤል "ምንም ኤሌክትሪክ፣ ውሃ እና ጋዝ እንዳያገኙ" በሚል መፈክር ጋዛን ሙሉ በሙሉ ክአገልግሎት ውጭ አድርጋለች ሲል አምነስቲ ከሷል።
ፍልስጤማውያን ለረሃብና በሽታዎች እንዲጋለጡ በማድረግ "በቀስታ እና በተሰላ ሞት" እንዲያልቁ ተደርጓልም ይላል።
የእስራኤል ባለስልጣናት እና ወታደሮች "ጋዛን ከምድረገጽ የማጥፋት" ንግግርና ንጹሃን ላይ ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች ከ44 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን አልቀውም አልቆመም ያለው የአምነስቲ ሪፖርት፥ አለማቀፉ ማህበሰብ የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴውን እንዲያስቆም አሳስቧል።
የመንግስታቱ ድርጅትን ኮንቬንሽን በመተላለፍ ለእስራኤል የጦር መሳሪያ የሚያቀርቡ ሀገራትም የዘር ፍጅቱ ተባባሪ ሆነዋል ነው ያለው።
እስራኤል በጋዛ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው በሚል የሚቀርቡባትን ወቀሳዎችና ክሶች በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጋለች። የፍልስጤሙ ሃማስ ንጹሃንን እንደ ሰብአዊ ጋሻ እየተጠቀመ መሆኑን በመጥቀስም ክሱን ወደ ቡድኑ ታዞራለች።
በ300 ገጾች የተዘጋጀው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምርመራ ሪፖርት ግን እስራኤል "የሃማስ ታጣቂዎች በማይገኙባቸው የንጹሃን መኖሪያና መገልገያ መሰረተ ልማቶችን ሆን ብላ በከባድ ፈንጂዎች ስታፈነዳ ቆይታለች" ብሏል።
የመብት ተሟጋች ድርጅቱ ከ1 ሺህ 200 በላይ እስራኤላውያንን የገደለው ሃማስ በፈጸማቸው ወንጀሎች ዙሪያ ያጠናቀረውን የምርመራ ሪፖርት በቅርቡ እንደሚያወጣ አስታውቋል።