ጠ/ሚ ዐቢይ “የሰው ልጆችን ህይወት የሚቀጥፍ ዘግናኝ ድርጊት አንታገስም” አሉ
ጠ/ሚ ዐቢይ “በንጹሃን ዜጎች ላይ በህገወጥና በኢ-መደበኛ ኃይሎች የሚደርስ ጥቃት ተቀባይነት የለውም” ብለዋል
በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ኢሰመኮና የኦሮሚያ ክልል አስታውቀዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “የሰው ልጆችን ህይወት የሚቀጥፍ ዘግናኝ ድርጊት የምንታገሰው አይደለም” ሲሉ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሰሞኑ በምእራብ ኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶችን ተከትሎ ነበማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባወጡት መግለጫ ነው ይህንን ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸውም፤ “በንጹሃን ዜጎች ላይ በህገወጥ እና በኢ-መደበኛ ኃይሎች የሚደርስ ጥቃት እና መተዳደሪያን ማውደም ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።
“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤኒሻንጉል እና ኦሮሚያ ክልሎች፣ ዋና ዓላማቸው ኅብረተሰቡን ማሸበር በሆነ አካላት የተፈጸመው የሰው ልጆችን ህይወት የሚቀጥፍ ዘግናኝ ድርጊት የምንታገሰው አይደለም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ጥቃት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሰላም እና ደህንነትን መመለስ አሁንም ቅድሚያ የምንሰጠው ተግባራችን ነው” ሲሉም አስታውቀዋል ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮማሽን (ኢሰመኮ) ትናንት ባወጣው መግለጫ ባሳለፍነው ቅዳሜ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ በመግስት እና መንግስት በሽብር በፈረጀው የሸኔ ታጣቂ ቡድን መካከል ከነበረውን ውጊያ ጋር በተያያዘ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።
ታጣቂ ቡድኑ በአካባቢው በሚኖሩ ሲቪል ሰዎች ላይ የህይወት፣ የአካል እና የንብረት ጉዳት ማድረሱን የገለጸው ኢሰመኮ የጸጥታ ሰጋት በመኖሩ ነዋሪዎቹ አሁንም ድጋፍ እየጠየቁ ነው ብሏል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤ በቀለ"መንግሥት በሲቪል ሰዎች ላይ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይፈጸም አስፈላጊ የሆኑ የመከላከል እርምጃዎችን እንዲወስድ"እና ሐችግሩ ዘለቂ መፍትሄ ኦንዲሰጥ አሳስበዋል።
የኦሮሚያ ክልል መንግስትም ባሳለፍነው ቅዳሜ ምሽት ባወጣው መግለጫ፤ “አሸባሪው የሸኔ ቡድን በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ባደረሰው ጥቃት በንጹሃን እና በንብረት ላይ ጉዳት አደርሷል” ብሏል።
የፌደራል እና የክልሉ የጸጥታ አካላት በሸኔ ቡድን ላይ የሚወስዱትን እርምጃ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያወጣው መግለጫ አመላክቷል።