በማይካድራ የደረሰውን ሰብአዊ ቀውስ ለማጣራት የምርመራ ቡድን ወደ ቦታው መላኩን ኢሰመኮ ገለጸ
በአፋጣኝ የሰብአዊ ዕርዳታ ጉዳይ ዴስክ እንዲያቋቁም እና ከሰብአዊ ዕርዳታ ድርጅቶች ጋር ምክክር እንዲጀመርም ጠይቋል
ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በአዲስ አበባ የታሰሩ ግለሰቦች የሰብአዊ መብት አያያዝ መልካም መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል
በማይካድራ የደረሰውን ሰብአዊ ቀውስ ለማጣራት የምርመራ ቡድን ወደ ቦታው መላኩን ኢሰመኮ ገለጸ
በማይካድራ የደረሰውን ሰብአዊ ቀውስ በአፋጣኝ ለማጣራት የምርመራ ቡድን ወደ ቦታው ማሰማራቱን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ። በሌሎች ቦታዎች የተፈጸሙ ማናቸውም የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችንም በተመሳሳይ መልኩ እንደሚመረምር እና የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥም እንደሚሰራ ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
ከግጭቱ ጋር በተያያዘ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መንግሥት እየወሰደ ባለው እርምጃ የታሰሩ ሰዎችን በሚመለከት እና በአንዳንድ አካባቢዎች ሰዎች በትግራይ ብሔር ማንነታቸው የተነሳ የማግለል እና መድልዎ አሰራር ደርሶብናል በማለት የገለጹትን መሰረት በማድረግ ኢሰመኮ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝም ነው የገለጸው።
ለኢሰመኮ ከቀረቡት ጥቆማዎች እና መረጃዎች ሰዎችን በብሄራቸው ማንነት በመለየት ለጥርጣሬ እና መድልዎ (ethnic profiling) እንዲጋለጡ የሚያደርግ ምክንያታዊ ስጋት መፈጠሩን በመረዳት ኮሚሽኑ ይህንንም በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝ ይፋ አድርጓል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም በቅርቡ የጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተፈጻሚነቱ ወሰን በትግራይ ክልል ውስጥ ብቻ ስለሆነ ፣ በሌሎች አካባቢዎች የሚደረግ የሕግ ማስከበር ሂደት መደበኛውን የሕግ ማስከበር ሥነ ሥርዓት ደንቦች ተከትሎ መፈጸም እንዳለበት አስታውሷል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በተመረጡ ፖሊስ ጣቢያዎች ፈጣን ክትትል በማድረግ ከወቅታዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎችን የእስር ሁኔታ መመልከቱንም የገለጸው ኢሰመኮ በተለይም በቦሌ፣ በካዛንቺስ፣ በአዋሬ፣ በተክለ ኃይማኖት እና በጨርቆስ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያዎች ተይዘው ይገኙ የነበሩ በድምሩ የ43 ታሳሪዎችን ሁኔታ አይቷል፡፡
እንዲሁም በፖሊስ ጥርጣሬ ተይዘው በዋስትና ስለተለቀቁ ሰዎች ከፖሊስ መረጃ የሰበሰበ ሲሆን አብዛኛዎቹ ሰዎች የተጠረጠሩበት ወንጀል ፈቃድ የሌለው የጦር መሳሪያ መያዝ የሚል እንደሆነ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ ሁሉም ተጠርጣሪዎች በወቅቱ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን እና አብዛኛዎቹ የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸው መለቀቃቸውንም ተረድቻለሁ ብሏል ኮሚሽኑ።
ኢሰመኮ ካነጋገራቸው ታሳሪዎች ውስጥ አንድ ሰው ብቻ በመጀመሪያ የያዛቸው ፖሊስ ደብድቦኛል ያሉ ሲሆን ፣ ፖሊስም ጉዳዩን የሚያጣራ መሆኑን እንዳረጋገጠ ነው ኮሚሽኑ የገለጸው፡፡ ከዚህ ውጪ ተጠርጣሪዎች “ፖሊስ በምርመራ ወቅት ምንም ጉዳት እንዳላደረሰባቸው፣ ዛቻ ወይም ማስፈራሪያ እንዳልገጠማቸው እና የእስር አያያዛቸውም ጥሩ መሆኑን ገልጸዋል” ሲልም አክሏል። በአንጻሩ የተወሰኑ ታሳሪዎች የተጠረጠሩት በብሄር ማንነታቸው ብቻ መሆኑን፤ አንዳንዶቹ ቤታቸው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ መበርበሩን እንደገለጹ ኮሚሽኑ አስረድቷል።
ኮሚሽኑ እንዳለው ፣ ፖሊስ በበኩሉ ሊሰወሩ የሚችሉ የጦር መሳሪያዎችን በአፋጣኝ ለመቆጣጠር በሕጉ መሰረት ከፍርድ ቤት በስልክ በተሰጠ የተፋጠነ ፍቃድ ብርበራ መካሄዱን ፣ አጠቃላይ ስራው በሕጋዊ ሥርዓት መመራቱን እና አብዛኛዎቹ ተጠርጣሪዎች በዋስትና መለቀቃቸውን አስረድቷል።
ከላይ እንደሚጣራ ከተገለፀው ፣ ድብደባ ደርሶብኛል ካሉት አንድ ተጠርጣሪ ውጭ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አለመኖሩን ኢሰመኮ እንደተገነዘበም ነው ኮሚሽኑ በመግለጫው ያስታወቀው፡፡ በሌላ በኩል በብሄር ማንነት በመለየት ለጥርጣሬ እና መድልዎ የመጋለጥ ስጋትን ለመቀነስ ጥንቃቄ እንዲደረግ ምክረ-ሃሳብ ሰጥቷል።
የሰብአዊ እርዳታ እና አገልግሎቶችን በአፋጣኝ ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳ ዘንድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና/ወይም በትግራይ ክልል በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ ኃይል በአፋጣኝ የሰብአዊ ዕርዳታ ጉዳይ ዴስክ እንዲያቋቁም እና ከሰብአዊ ዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ጋር ምክክር እንዲጀመርም ኢሰመኮ ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም ቀይ መስቀል ማህበር ሰብአዊ አገልግሎቶችን ማከናወን እንዲችል በውጊያው ተሳታፊ የሆኑ አካላት ተፈፃሚነት ባላቸው ዓለምአቀፍ ሕጎች መሰረት የቀይ መስቀል አርማን እንዲያከብሩና ተገቢውን ትብብር እንዲያደርጉሲልም አሳስቧል፡፡
የትግራይ ክልል ኃይል በሰሜን ዕዝ በሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካሳወቁ በኋላ የተጀመረው ውጊያ ዛሬ 12ኛ ቀኑን ይዟል፡፡ በዚህም ሂደት ሰብዓዊ ጥቃቶች እየደረሱ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን በተለይ በማይካድራ ቁጥራቸው በግልጽ ያልታወቀ በርካታ ንጹኃን የተገደሉበት ክስተት በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ግድያው በሕወሓት ታማኝ ኃይሎች ስለመፈጸሙ ከምስክሮች ማረጋገጡን አምነስቲ ኢንተርናሺናል ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡