ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በከፍተኛ ደረጃ ማሻቀቡ ተገለጸ
ከሰሀራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት የዚህ ወንጀል ተጠቂ የሆኑ በርካታ ዜጎች መነሻ በመሆን ቀዳሚዎቹ ናቸው
በህገወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎች ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሚጓዙ ሰዎች በ25 በመቶ አድጓል ነው የተባለው
በግጭት፣ በአየር ንብረት ምክንያት በተከሰቱ አደጋዎች እና በአለም አቀፍ ቀውሶች ምክንያት ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
ወንጀለኞች ሰዎችን ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በህገወጥ መንገድ በማዘዋወር ለከፍተኛ የጉልበት ብዝበዛ ፣ ለወሲባዊ ባርነት እና በሌሎችም ህገወጥ ተግባራት ላይ እያሰማሯቸው ይገኛሉ ተብሏል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ መቀዛቀዝ በኋላ ይህ ህገወጥ ድርጊት በከፍተኛ ደረጃ ማንሰራራቱን የገለጸው የተመድ ሪፖርት በህገወጥ ዝውውሮች ውስጥ ቀዳሚ ተጠቂ የሆኑት ሴቶች 39 በመቶ እንደሚሸፍኑ ጠቅሷል፡፡
ከሴቶች ቀጥሎ ህጻናት 38 በመቶውን የሚሸፍኑ ሲሆን ወንዶች በ23 በመቶ እንደሚገኙ ተመላክቷል፡፡
የኮሮና ቫይረስ በነበረበት ወቅት የህገወጥ የሰዎች ዝውውር በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶ የነበረ ሲሆን ከ2022 ጀምሮ ግን መጠኑ ድጋሚ እየጨመረ መሆኑ ሲነገር በዚሁ አመት ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች የዚህ ወንጀል ሰለባ ሆነዋል፡፡
ሴቶች እና ልጃገረዶች ከሚዘዋወሩበት የተለመዱ ምክንያቶች መካከል 60 በመቶ እና ከዚያ በላይ የሚሆነው ከወሲብ ባርነት እና ከጉልበት ብዝበዛ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡
ህጻናት እና አዋቂ ወንዶችን በተመለከተ ደግሞ የግዳጅ ወንጀል ፣ ዝርፍያ እና የግዳጅ ልመናን ያካትታሉ።
በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እጅ የሚወድቁ ህጻናት ቁጥር መጨመር ወደ አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ ለብቻቻው የሚሰደዱ ህጻናት ቁጥር ማሻቀብ ጋር ሊገናኝ እንደሚችል ሪፖርቱ ገልጿል፡፡
ውስብስብ የህገወጥ የሰዎች ማዘዋወሪያ መስመሮች የተዘረጉባት አፍሪካ ቀዳሚው ተጠቂ ስትሆን ከሰሀራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ 26 በመቶ ድርሻ አላቸው ተብሏል፡፡
ከሰሀራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት በተጨማሪ ሰሜን አሜሪካ ፣ ምዕራብ እና ደቡብ አውሮፓ ቀጠናዎች ድርጊቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረባቸው የሚገኑ ናቸው፡፡