ወታደራዊ ህግ ያወጁት የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝደንት ዩን ቢሮ በፖሊስ ተበረበረ
የአሜሪካ አጋር የሆነችው ደቡብ ኮሪያ ፕሬዝደንት ዩን ባለፈው ሳምንት ወታደራዊ ህግ ማወጃቸውን ተከትሎ ጥልቅ ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው
ፕሬዝደንት ዩን አመጽ በማስነሳት ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ እየተካሄደባቸው እና ከሀገር እንዳይወጡ እግድ የተጣለባቸው ቢሆንም እስካሁን አልታሰሩም
ወታደራዊ ህግ ያወጁት የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝደንት ዩን ቢሮ በፖሊስ ተበረበረ።
የደቡብ ኮሪያ ፖሊስ በዛሬው እለት የፕሬዝደንት ዩን ሱክ የኦልን ቢሮ መበርበሩን እና ከስልጣን የተነሱት ሚኒስትር ራሳቸውን ለማጥፋት መሞከራቸውን ባለስልጣናትን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።
የአሜሪካ አጋር የሆነችው ደቡብ ኮሪያ ፕሬዝደንት ዩን ባለፈው ሳምንት ወታደራዊ ህግ ማወጃቸውን ተከትሎ ጥልቅ ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው።
ብርበራው በእስያ አህጉር በኢኮኖሚዋ አራተኛ የሆነችውን ሀገር ህገመንግስታዊ ቀውስ ውስጥ ባስገባው በድንገት በታወጀው ወታደራዊ ህግ ላይ እየተደረገ ያለው ምርመራ መጠናከሩን ያሳያል ተብሏል።
የፍትህ ሚኒስትር ባለስልጣን እንደተናገሩት የዩን የቅርብ ሰው እና የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ኪም ዮንግሂዩን ባለፈው እሁድ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በታሰሩበት ቦታ በሸሚዛቸው እና በውስጥ ልብሳቸው ራሳቸውን ለማጥፋት ሙከራ አድርገዋል።
ባለስልጣኑ አክለውም ኪም አሁን ክትትል እየተደረገባቸው ነው ብለዋል።
ኪም ለአጭር ጊዜ ለቆየው ወታደራዊ አዋጅ ኃላፊነቱን እሳቸው ብቻ እንደሚወስዱ በመግለጽ ለነበራቸው ሚኒ ይቅርታ ጠይቀው በገዛ ፈቃዳቸው ነበር ስልጣን የተቀቁት።
ዩን በድንገት ወታደራዊ አዋጅ ማወጃቸውን ተከትሎ የራሳቸውን ፓርቲ የፓርላማ አባላትን ጨምሮ አዋጁን ወዲያውኑ እንዲሰርዙት ጠይቀዋቸዋል። ፕሬዝደንቱም ከሰአታት በኋላ አዋጁን በይፋ ሰርዘውታል፤ ይቅርታም ጠይቀዋል።
ፕሬዝደንት ዩን አመጽ በማስነሳት ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ እየተካሄደባቸው እና ከሀገር እንዳይወጡ እግድ የተጣለባቸው ቢሆንም እስካሁን አልታሰሩም፤ በባለስልጣናትም አልተጠየቁም።
ፕሬዝደንት ከባለፈው እሁድ ጀምሮ በአደባባይ አለመታየታቸው እና ብርብራው ሲደረግም ቢሮ ውስጥ አልነበሩም ተብሏል።
የደቡብ ኮሪያው ዮንሀፕ ዜና አግልግሎት እንደዘገበው የፖሊስ መርማሪዎች ባቀረቡት የፍተሻ ፍቃድ ላይ የዩን ስም በግልጽ ተጠቅሷል።
የፓርላማ አባለት ወደ ፓርላማ እንዳይገቡ አድረጓል የተባለው የብሔራዊ ፖሊስ ኃላፊ ቾ ጂሆ በዛሬው እለት ጠዋት መታሰሩን ዘገባው ገልጿል።
ፕሬዝደንት ዩን ይታሰሩ የሚለው ጫና የበረታው ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ወታደሮች ወደ ፓርላማ እንዲገቡ እና ወታደራዊ ህጉን ውድቅ ለማድረግ የሚገቡትን የፓርላማ አባላት እንዲያስቆሙ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ከገለጹ በኋላ ነው።
የልዩ ኃይል አዛዥ የሆኑት ክዋክ ጅንግ ጂዩን ዩን ወታደሮች "አሁኑኑ ሰብረው እንዲገቡ እና የፓርላማ አባላትን እንዲያስወጡ" ትዕዛዝ መስጠታቸውን በትናንትናው እለት ለፓርላማ ተናግረዋል።
ገዥው 'ፓርቲ ፕፕል ፓወር ፓርቲ' (ፒፒፒ) ሊቀመንበር ዩን በስርአት ከስልጣን የሚለቁበት መንገድ እንደሚመቻች እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሀን ዱክ ሶ ሀገራዊ ጉዳዮችን እንደሚቆጣጠሩ ገልጸዋል።