ኢትዮጵያ በእርዳታ ስርጭት ላለመሳተፍ መስማማቷ ተገለጸ
ካሳለፍነው ግንቦት ጀምሮ በኢትዮጵያ የረድኤት ድርጅቶች እርዳታ መስጠት አቋርጠዋል
የእርዳታ መሰረቅ ለረድኤት ድርጅቶች ስራ ማቆም ዋነኛው ምክንያት ነበር
ኢትዮጵያ በእርዳታ ስርጭት ላለመሳተፍ መስማማቷ ተገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ካሳለፍነው ግንቦት ወር ጀምሮ የመጋዝን ስርቆት ተፈጽሞብናል በሚል እርዳታ መስጠት አቁመው ነበር፡፡
እርዳታ መቆሙን ተከትሎም ስደተኞች እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ረሀብን ጨምሮ ተረጂዎች ህይወታቸውን እስከማጣት መድረሳቸው በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
በእርዳታ እህል ስርቆቱ ላይ የፌደራል እና የክልል መንግስታት ባለስልጣናት እጃቸው እንዳለበት በወቅቱ በረድኤት ድርጅቶቹ በኩል ተገልጾም ነበር፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ለተረጂዎች የተቀመጠን እህል ወደ ጎረቤት ሀገር ይላክ እንደነበርም የተገለጸ ሲሆን የፌደራል መንግስት በወቅቱ የቀረበበትን ክስ ውድቅ አድርጓል፡፡
የአሜሪካ የልማት ተራድዖ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ዛሬ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ ያቋረጠውን የምግብ እርዳታ ዳግም ለማስጀመር መወሰኑን አስታውቋል፡፡
እርዳታው የተጀመረው የኢትዮጵያ መንግስት ከእርዳታው ጋር በተያያዘ በስርጭቱ ላይ እጁን እንደማያስገባ ከተስማማ በኋላ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የምግብ እርዳታ 'ለተቸገሩ ሰዎች እየደረሰ አይደለም' በሚል አቆመች
ይሁንና ዩኤስኤአይዲ በኢትዮጵያ ያቋረጠውን የምግብ እርዳታ ለመቀጠል የወሰነው ለስደተኞች ብቻ እንደሆነ አስታውቋል።
ድርጅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት እና አጋሮቹ የስደተኞች የምግብ እርዳታ አቅርቦት መዋቅር ላይ ለውጦችን በማድረጋቸው እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሱን ገልጿል፡፡
“የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ ለሚገኙ ስደተኞች የምግብ እርዳታን በማጓጓዝ፣ በማከማቸት እና በማከፋፈል ዙሪያ ምንም አይነት ተሳትፎ እንደማይኖረው ስምምነት ላይ በመደረሱ የእርዳታ እህል አቅርቦቱን ለመስጀመር መወሰኑን ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ከሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ እና ሌሎች አከባቢዎች የመጡ አንድ ሚሊዮን ስደተኞች ይኖራሉ የተባለ እርዳታው ለነዚህ ሰዎች ብቻ ይሰጣል ተብሏል፡፡
የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያዊያን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እርዳታው ለተረጂዎች ብቻ የሚደርስበት መንገድ እስከሚመቻች ድረስ ተቋርጦ እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ በተከሰተው በጦርነት፣ ድርቅ እና ሌሎች አደጋዎች ምክንያት የተረጂዎች ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ ሲሆን አሁን ላይ ከ25 ሚሊዮን በላይ ዜጎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተመድ ሪፖርት ያስረዳል፡፡