ፖለቲካ
ኢትዮጵያና አሜሪካ ከተቸገሩ ሰዎች ተነጥቋል የተባለውን የምግብ እርዳታ እየመረመርን ነው አሉ
ሀገራቱ እርዳታውን ወደ ሌላ ቦታ አሽሽተዋል የተባሉ ወንጀለኞች በህግ እንዲጠየቁ እናደርጋለን ብለዋል
አሜሪካ የምግብ እርዳታው በተስፋፋና በተቀናጀ መልኩ ወጀ ሌላ አቅጣጫ እየተወሰደ ነው ብላለች
ከሰሞኑን አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው የምግብ እርዳታ ለተቸገሩ ሰዎች እየደረሰ አይደለም በሚል ማቆሟን አስታውቃለች።
- አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የምግብ እርዳታ 'ለተቸገሩ ሰዎች እየደረሰ አይደለም' በሚል አቆመች
- እርዳታ ወደ ትግራይ በመግባቱ ተቃውሞ ባይኖረውም ድጋፉ ፍትሀዊ እንዲሆን የአማራ ክልል ጠየቀ
በጉዳዩ ላይ ሁለቱ ሀገራት የጋራ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፤ የምግብ እርዳታውን ውጥንቅጥ ለመፍታት ቁርጠኛ ነን ብለዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር እና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለውን አሳሳቢ የምግብ እርዳታ ለተጎጅዎች ያለመድረስ ችግር ለመፍታት ቁርጠኝነት እንዳላቸው አስታውቀዋል።
ሁለቱ ሀገራት እርዳታውን ወደ ሌላ ቦታ ዘውረዋል የተባሉ ወንጀለኞች በህግ እንዲጠየቁ ምርመራ እያደረግን ነው ብለዋል።
ሀገራቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ቀልጣፋ የእርዳታ ማከፋፈያ ስርዓትን ለማስፈን በትብብር ለመስራትም ቃል ገብተዋል።
ይህም ስርዓት እርዳታ ከተጎጅዎች እንዳይወሰድ ይጠብቃል ሲል የጋራ መግለጫው ጠቅሷል።
በአዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በኩል የወጣው መግለጫው፤ አሜሪካ እና ኢትዮጵያ ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ጥቅም ሲሉ አጋርነታቸውን ቀጥለዋል ብሏል።
መግለጫው ለተሻሉ እድሎችና ግንኙነቱ የጋራ ጥቅሞችን በሚያስቀድም መልኩ በጋራ ለመስራት ቁርጠኞች ነን ማለታቸውን ጠቅሷል።