ቻይና ሮቦቶች ከሰዎች ጋር የሚፎካከሩበትን የግማሽ ማራቶን ሩጫ ውድድር ልታዘጋጅ ነው
በመጪው ሚያዚያ ይካሄዳል በተባለው ውድድር እስከ ሁለት ሜትር ቁመት ያላቸው ሮቦቶች ይሳተፉበታል
የተወዳዳሪ ሮቦቶቹ ፍጥነት በስአት ከስምንት እስከ አስራሁለት ኪሎሜትር እንደሚደርስ ተነግሯል
ቻይና ሰው መሰል ሮቦቶች እና ሰዎች የሚወዳደሩበት የግማሽ ማራቶን ሩጫ ውድድር ልታዘጋጅ መሆኑን አስታወቀች፡፡
በውድድሩ ላይ 12 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ከተለያዩ አለም አቀፍ ሮቦት አምራቾች ከተውጣጡ ሮቦቶች ጋር ለሜዳሊያ የሚወዳደሩ ይሆናል፡፡
የቻይናው ኢኮኖሚ ቴክኖሎጂ ልማት ማዕከል ውድድሩን በመጪው ሚያዝያ ለማዘጋጀት ያቀደ ሲሆን ሰዎች ከሮቦቶች ጋር በሚያደርጉት ውድድር አዲስ ልምድን ያገኛሉ ብሏል፡፡
የኢለን መስኩ ቴስላ፣ ቦስተን ዳይናሚክስ እና 1Xን ጨምሮ በዚህ እንግዳ በሆነ ውድድር ላይ የተለያዩ የሮቦት አምራች ኩባንያዎች ሮቦቶቻቸውን ይወክላሉ፡፡
ተሳታፊ ሮቦቶች ሰው መሰል (ሂዩማኖይድ) የተሰኙት ሲሆን ቀለል ካሉ የብረት አይነቶች እንዲዘጋጁ እና ቁመታቸው ከ0.5 እስከ 2 ሜትር እንደሚሆን አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የመሮጥ ወይም ቢያንስ በሁለት እግሮች የመራመድ ችሎታ ሊኖራቸው ይገባል፤ አሸናፊዎቹ ሰውም ይሁን ሮቦት እንደ ደረጃቸው የገንዘብ ሽልማት ያገኛሉ።
ሮቦቶቹ ሰዎችን የማሸነፋቸው እድል ጥያቄ ውስጥ ገብቷል ነገር ግን የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ሮቦቶቹ ልምድ ላላቸው ሯጮች ብርቱ ተፎካካሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
የሮቦቶቹ ፍጥነት በሰአት ከ8 እስከ 12 ኪሎ ሜትር እንደሚደርስ የተገለፀ ሲሆን፤ 21 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የግማሽ ማራቶን ውድድርን በአንድ ሰአት ተኩል ውስጥ ለማጠናቀቅ በአማካይ በሰአት 14 ኪሎሜትርን መሸፈን መቻል አለባቸው፡፡
በተጨማሪም የባትሪ ቆይታ ለውድድሩ ተግዳሮት ሊሆን የሚችል ጉዳይ ነው አዘጋጆቹ በውድድሩ አጋማሽ ላይ ባትሪ መቀየር እንደሚፈቀድ አስታውቀዋል።
ሮቦቶች በሩጫ ዝግጅቶች ላይ ሲወዳደሩ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፤ ባለፈው አመት በደቡብ ኮሪያ የተሰራው ላይቦ 2 ባለ አራት እግር ሮቦት በአንድ ቻርጅ ሙሉ ማራቶን በማጠናቀቅ የመጀመሪያው ሮቦት መሆን ችሏል፡፡
የሚያዚያው ውድድር ለባለ ሁለት እግር ሮቦቶች ብቻ የተዘጋጀ መሆኑን ተከትሎ የደቡብ ኮሪያው ሮቦት በቤጂንጉ ሩጫ ላይ እንደማይሳተፍ ታውቋል፡፡