ሰልፉ ዋነኛው የፕሬዝዳንት ፑቲን ተቃዋሚ አሌክሲ ናቫልኒ እንዲፈታ የሚጠይቅ ነው
በሩሲያ በተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ሰልፈኞቹ ከሀገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች ጋር መጋጨታቸው ተሰማ፡፡
ሰልፈኞቹ ከፖሊስ ጋር በነበራቸው እሰጥ አገባ በርካቶች ለእስር መዳረጋቸውን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡
የተቃውሞ ሰልፉ የተጠራው በሩሲያ ዋነኛ የሚባለው የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪ አሌክሲ ናቫልኒ መታሰሩን በመቃወም መሆኑንም ነው ከሞስኮ የወጡ ዘገባዎች የሚያመለክቱት፡፡
ነርቩ ተመርዞ የነበረው ናቫልኒ ፣ ለህክምና በጀርመን ቆይቶ ወደ ሀገሩ በተመለሰበት ቅጽበት በቀጥታ ለእስር መዳረጉ ይታወሳል፡፡ ይህንን ተከትሎም የፖለቲከኛው ደጋፊዎች ናቫልኒ ከእስር እንዲለቀቅ የሚጠይቅ የተቃውሞ ሰልፍ ጠርተዋል፡፡
ናቫልኒ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ከሚቃወሙ ፖለቲከኞች ዋነኛውና ግንባር ቀደሙ ሲሆን ከስድስት ቀን በፊት ነው ከአውሮፕላን ማረፊያ ወደ እስር ቤት የገባው፡፡
ለአምስት ወራት በጀርመን ህክምና ላይ የነበረው ፖለቲከኛው ፣ የህመሙ መነሻ የሆነው የነርቭ መመረዝ በክሬሚሊን ሰዎች የተቀነባበረ እንደነበር ቀደም ሲል ሲወራ ቆይቷል፡፡
በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች አደባባይ ወጥተው ናቫልኒ እንዲፈታ መጠየቃቸውን ኢንዲፐንደንት ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
በቭላድቮስቶክ የተጀመረው ይህ የተቃውሞ ሰልፍ በሌሎች አካባቢዎችም የቀጠለ ሲሆን ሰልፈኞች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል፡፡
እስካሁን በተጠናቀረ መረጃ መሰረት ከ1,000 በላይ ሰዎች መታሰራቸውም የተገለጸ ሲሆን ከነዚህ ውስጥም ጋዜጠኞችና የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ይገኙበታል ተብሏል፡፡
የሰልፉ ጥሪ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ፖሊስ እስር ጀምሮ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ ፖሊስ ሰልፈኞቹ የሚገናኙበትን የፑሽኪን አደባባይን በጥብቅ ቁጥጥር ስር አድርጎ ሰልፉ እንዳይካሄድ መከላከሉንም ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ በዚህ የተቃውሞ ሰልፍ የአሌክሲ ናቫልኒ ባለቤት ዩሊያ ናቫልኒም ለእስር ተዳርጋለች ተብሏል፡፡ የአሁኑተቃውሞ በክሬሚሊን ቤተመንግስትና በተቃዋሚዎች መካከል የሚደረገው ፉክክር መጀመሩን ያመለክታል እንደሚያመለክት ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡