የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና ሩሲያ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ
በኮሮናቫይረስ ክትባት ሙከራዎች ላይ በትብብር በመስራት ላይ መሆናቸውን አሳውቀዋል
የሁለቱ ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በኮሮና ቫይረስ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሩሲያ አቻቸው ሰርጊ ላቭሮቭ ጋር በሩሲያ ተገኛኝተው ተነጋግረዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ከሩስያ ጋር ባላት ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ደስተኛ መሆኗን የዩኤኢ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብዱላሂ ቢን ዛይድ አል ናህያን ተናግረዋል፡፡ ሞስኮ እና አቡ ዳቢ በሩስያ በበለጸገው ስፑትኒክ ቪ የኮሮናቫይረስ ክትባት ሙከራዎች ላይ በትብብር በመስራት ላይ መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የሩስያውን ስፑትኒክ ቪ ክትባት ሶስተኛ ደረጃ ክሊኒካዊ ሙከራ በማጠናቀቅ ላይ መሆኗንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ሼክ አብዱላሂ ቢን ዛይድ አል ናህያን
ሁለቱ ሚኒስትሮች ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተጨማሪ በሊቢያ ፣ በሶሪያ እና በአረብ-እስራኤል ግንኙነት እንዲሁም በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
የሊቢያን ቀውስ ለመፍታት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የላቀ ሚና እንድትወጣ የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጊ ላቭሮቭ ጠይቀዋል፡፡
“የሊቢያ ፖለቲካ በጽንፈኞች እጅ ላይ ወድቋል” ያሉት የዩኤኢው ሼክ አብዱላሂ በሀገሪቱ እና በቀጣናው ጽንፈኝነትን መከላከል ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት አስቸኳይ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የአረብ ሀገራት እና እስራኤል የደረሱትን የሰላም ስምምነት ያደነቁት ላቭሮቭ በእስራኤል እና ፍልስጤም መካከል ቀጥተኛ የሰላም ድርድር ሊደረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ሀገራቸው የሁለት ሀገር መፍትሔን እንደምትደግፍም ነው የገለጹት፡፡
ሁለቱ ሀገራት በቀጣይነት ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማሳደግ እና የመካከለኛውን ምስራቅ ቀጣናዊ ችግሮች ለመፍታት በጋራ እንደሚሰሩ ቆርጠው መነሳታቸውን ሚኒስትሮቹ በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል አል አረቢያ እንደዘገበው፡፡