በሳኡዲ አረቢያ በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት 550 ሃጃጆች መሞታቸው ተሰማ
ከሟቹቹ መካከል ከ300 በላይ የሚሆኑት የግብጽ ዜጎች ናቸው
በሳምንቱ መጀመርያ ቀን ሰኞ በሳኡዲ 58.8 ዲግሪ ሴሊሺየስ ሙቀት ተመዝግቧል
አመታዊውን የሀጂ ስነስርአት ለመካፈል ወደ ሳኡዲ ካቀኑ ሰዎች መካከል ከ550 በላይ ሰዎች በሙቀት መሞታቸው ተሰምቷል፡፡
ከከፍተኛ የሙቀት መዕበል ጋር በተያየዘ በሚፈጠሩ በሽታዎች ነው ሃጃጆቹ ህይወታቸው ያለፈው፡፡ ከሟቾቹ መካከል 323 የግብጽ ፣ 144 የኢንዶኔዢያ፣ 35 የቱኒዝያ ፣ 11 የኢራን ፣ 6 የሴኔጋል ዜግነት ያላቸው ሃጃጆች ናቸው ተብሏል፡፡
የሟች ቤተሰቦች በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሳኡዲ ሆስፒታሎች ዘመዶቻቸውን በማፈላለግ ላይ ሲሆኑ ዮርዳኖስ በበኩሏ በሃጂ የሞቱ ዜጎቿን ለመቀበር 41 የመቃብር ስፍራዎችን ማዘጋጀቷን በትላንትናው እለት አስታውቃለች፡፡
የዘንድሮው የሀጂ ስነስርአት ከ1.8 ሚሊዮን በላይ የእስልምና እምነት ተከታዮች የተካፈሉበት ሲሆን ከሰሞኑ በተለያዩ የአለም ክፍላት በተደጋጋሚ የተፈጠረው የሙቀት ማዕበል በሳኡዲም ለሃጃጆች ፈታኝ እንደሚሆን ሲነገር ሰንብቷል፡፡
የሳኡዲ የጤና ሚንስቴር ከሟቾቹ መካከል አብዛኛዎቹ አድሜያቸው የገፋ እና የጤና እክል የነበረባቸው ሃጃጆች መሆናቸውን ገልጾ ከሙቀት ማእበሉ ጋር በተገናኝ የታመሙ 2700 ሃጃጆች የጤና ክትትል እየተደረጋላቸው እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡
ሚንስቴሩ ሀጃጆች በሚንቀሳቀሱበት ስፍራ ጃንጥላ እንዳይለያቸው እንዲሁም ከፍተኛ ሙቀት በሚኖርበት ከረፋዱ 5 - እስከ 9 ሰአት ድረስ በቤት ውስጥ እንዲቀመጡ ማስጠንቀቂያዎችን ሲያስነግር መሰንበቱን ነው የተናገረው፡፡
በባለፈው አመት ከሙቀት ጋር በተያያዘ እና በተለያዩ ችግሮች ከ240 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል፡፡
በተጨማሪም በ2015 በተፈጠረ ከፍተኛ መጨናነቅ ከ2000 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ ከ400 በላይ የሚሆኑት ደግሞ የደረሱበት መጥፋቱ ተነግሮ ነበር፡፡ ይህም በሀጂ ታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው የሞተበት አጋጣሚ እንደነበር ተገልጿል
ባሳለፍነው አርብ የተጀመረው የሀጂ ስነስርአት በዛሬው እለት በካአባ ዙርያ በሚከናወን ሀይማኖታዊ ስነስርአት የሚጠናቀቅ ሲሆን ሃጃጆች ከነገ ጀምሮ ወደየመጡበት ሀገር መመለስ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የእስልምና ሀይማኖት ከሚያዛቸው አምስቱ መሰረታዊያን መካከል አንዱ የሆነውን የሀጂ ስነስርአት ለመከወን በየአመቱ በሚሊየን የሚቆጠሩ የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ወደ ሳኡዲ ያቀናሉ፡፡ የኮሮና ቫይረስ ከመከሰቱ አስቀድሞ በ2019 2.5 ሚሊየን ሃጃጆች ሀይማኖታዊ ስነስርአቱን አከናውነዋል፡፡