በሃውቲዎች ጥቃት የደረሰባት መርከብ በቀይ ባህር መስመጧ ተነገረ
የላይቤሪያ ሰንደቅ አላማ የምታውለበልበውና በግሪክ ኩባንያ የምትተዳደረው መርከብ ባለፈው ሳምንት ነበር በውሃ ውስጥ በሚጓዝ ድሮን ጥቃት የተፈጸመባት
በመጋቢት ወርም ማዳበሪያ የጫነችው የብሪታንያ መርከብ በቀይ ባህር መስጠሟ ይታወሳል
በየመኑ ሃውቲ ታጣቂ ቡድን ባለፈው ሳምንት ጥቃት የተፈጸመባት መርከብ መስጠሟ ተነገረ።
የላይቤሪያን ሰንደቅ አላማ የምታውለበልበውና የግሪኩ “ቱተር” ኩባንያ ንብረት የሆነችው መርከብ በቀይ ባህር መስመጧን የብሪታንያ የማሪታይም ንግድ አስተዳደር አስታውቋል።
“ቁርጥራጮች እና የሚፈስ ነዳጅ መርከቧ ለመጨረሻ ጊዜ በታየችበት አካባቢ ታይቷል” ያለው ተቋሙ፥ ይህም መርከቧ መስጠሟን እንደሚያመላክት ገልጿል።
ሃውቲዎች ከሰባት ቀናት በፊት በውሃ ውስጥ በሚጓዝ ድሮን ጥቃት የተፈጸመባት “ቱተር” መርከብ ስለመስመጧ እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጡም ብሏል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።
ጥቃቱ ሲፈጸም በመርከቧ የሞተር ክፍል ውስጥ የነበረ ፊሊፒናዊ መርከበኛ ህይወቱ ማለፉን የአሜሪካ ባለስልጣናት ቢገልጹም ማኒላ እስካሁን ያለችው ነገር የለም።
በቀይ ባህር በሃውቲዎች ጥቃት መርከብ ሲሰጥም የ”ቱተር” ሁለተኛው ነው።
ባለፈው መጋቢት ወር ማዳበሪያ የጫነችው የብሪታንያ “ሩብይማር” መርከብ በቀይ ባህር መስመጧ ይታወሳል።
እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን ድብደባ የሚቃወሙት የሃውቲ ታጣቂዎች ከእስራኤል፣ አሜሪካና ብሪታንያ ጋር ግንኙነት አላቸው ባሏቸው መርከቦች ላይ ከ50 በላይ ጥቃቶችን ፈጽመዋል።
ዋሽንግተን ከጥር ወር ጀምሮ አጋሮቿን አስተባብራ በቡድኑ ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃት ስትፈጽመ መቆየቷ ይታወሳል።
ከትናንት በስቲያም በሆዴይዳህ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እና በካማራን ደሴት አቅራቢያ ከብሪታንያ ጋር የአየር ድብደባ መፈጸሟን ነው ሬውተርስ የዘገበው።
ይሁን እንጂ የዋሽንግተን እና ለንደን ድብደባ የሃውቲ ታጣቂዎችን አንድ መርከብ ከመያዝና ሁለት ከማስመጥ አልገታቸውም።
የቡድኑ የድሮን እና ሚሳኤል ጥቃት የመርከብ ኩባንያዎች አቋረጩን የስዊዝ ካናል እየተው በረጅሙ የኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ (ደቡብ አፍሪካ) መስመር እንዲጓዝ አድርጓቸዋል።
የአሜሪካ የመከላከያ ደህንነት ተቋም በቅርቡ ያወጣው ሪፖርትም በቀይ ባህር የሚያልፉ እቃ የጫኑ መርከቦች ቁጥር ከታህሳስ ወር ወዲህ በ90 በመቶ መቀነሱን ነው የጠቆመው።