እስራኤል በሐማስ ለታገቱባት እያንዳንዱ ዜጎች አምስት ሚሊዮን ዶላር እከፍላለሁ አለች
የፍልስጤሙ ሐማስ ከአንድ ዓመት በፊት 250 እስራኤላዊንን አግቶ መውሰዱ ይታወሳል
ከታገቱ 250 እስራኤላዊን መካከል 97ቱ አሁንም በሐማስ እጅ ስር ይገኛሉ
እስራኤል በሐማስ ለታገቱባት እያንዳንዱ ዜጎች አምስት ሚሊዮን ዶላር እከፍላለሁ አለች፡፡
ከ13 ወራት በፊት ለፍልስጤም ነጻነት እንደሚታገል የገለጸው ሐማስ በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ተቀስቅሷል፡፡
እስራኤል ይህን ጦርነት የምታቆመው ሁሉንም ታጋቾች እስከምታስለቅቅ እና ሐማስ ዳግም ለእስራኤል ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ከተመታ በኋላ መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጻለች፡፡
ባለፉት ጊዜያትም ከታገቱት 250 ዜጎች ውስጥ 34ቱ መሞታቸው ሲረጋገጥ 97ቱ አሁንም በሐማስ እገታ ስር መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በፍልስጥሟ ኔትዛሪም ሆነው ባደረጉት ንግግር የታገቱ እስራኤላዊያንን ለማስለቀቅ 5 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
የእስራኤል ጦር ታጋቾችን ከነ ህይወታቸው አልያም አስከሬናቸውን ስለቀቅ ጥቃቱን እንደሚቀጥልም ተገልጿል፡፡
በሐማስ ለታገቱ እያንዳንዳቸው እስራኤላዊያን 5 ሚሊዮን ዶላር እንደሚከፈል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡
የአደጋ እና ጥይት መከላከያ አልባሳትን ለብሰው በጦር ማዘዣ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐማስ ዳግም ጋዛን ማስተዳደር እንደማይችልም ተናግረዋል፡፡
በእስራኤል-ሐማስ ጦርነት ምክንያት ከፍልስጤም በኩል ከ43 ሺህ በላይ ዜጎች ሲገደሉ በእስራኤል በኩል ደግሞ 1 ሺህ 200 ንጹሃን መገደላቸውን የተመድ ሪፖርት ያስረዳል፡፡