የሃንጋሪ ጠቅላይ ሚኒሰትር የሩሲያ ዩክሬን ጦርነትን ለማቆም ሩሲያና አሜሪካ ድርድር እንዲያደርጉም ጠየቁ
ጠቅላይ ሚኒሰትር ኦርባን የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ውጤታማ አይደለም አሉ
ኦርባን፡ ዩክሬን ጦርነቱን አሁን በተያዘችበት መንገድ በጭራሽ አታሸንፍም ብለዋል
የሃንጋሪ ጠቅላይ ሚኒሰትር ኦርባን የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ውጤታማ አይደለም አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሞስኮ ላይ የተጣለው የቅጣት ማዕቀብ ውጤታማ ባለመሆኑ ህብረቱ በዩክሬን ጦርነት ላይ ሊከተለው የሚገባ አዲስ ስልት ያስፈልገዋል ሲሉም ተናግረዋል።
“ጦርነቱን ከማሸነፍ ይልቅ…. በሰላም ንግግሮች ላይ የሚያተኩር እና ጥሩ የሰላም ፕሮፖዛል የሚረቀቅበት አዲስ ስልት ያስፈልጋል” ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ኦርባን በአውሮፓ ውስጥ ያሉ መንግስታት "እንደ ዶሚኖዎች" እየፈራረሱ በመሆናቸው ይህ ስትራቴጂ አልተሳካም ፣ የኃይል ዋጋ ጨምሯል እና አሁን አዲስ ስትራቴጂ ያስፈልጋል ሲሉም ተደምጠዋ።
"በአራቱም ጎማዎች ቀዳዳ ባለው መኪና ውስጥ ተቀምጠናል፣ ጦርነቱ በዚህ መንገድ ማሸነፍ እንደማይቻል ፍጹም ግልጽ ነው" ሲሉም አክለዋል።
ዩክሬን ጦርነቱን በዚህ መንገድ በጭራሽ አታሸንፍም "የሩሲያ ጦር ያለው የበላይነት ብቻ ለዚህ በቂ ነው" ያሉት ኦርባን ፤ ጦርነቱን ለማቆም ሩሲያ እና አሜሪካ ድርድር እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር የአውሮፓ ህብረት ሩሲያ በተለይም የሩሲያ ጋዝ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ በሚል እገዳዎች በጣለበት ወቅት፣ የሀገራቸውን ኢኮኖሚ ያዳክማል በሚል እርምጃውን መቃወማቸው የሚታወስ ነው።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን አውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ የጣለውን ከባድ ማዕቀብ እስከ ጥር 2023 ማራዘሙን በቅረቡ ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
ሞስኮ ለጥቃቱ ከፍተኛ ዋጋ መክፈሉን መቀጠል አለባት ሲሉም ነበር የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን በወቅቱ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ የገለጹት።
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ እና የደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፕ ቦሬል በበኩላቸው “የአውሮፓ ህብረት ማዕቀቦች ጠንካራ እና ከባድ ናቸው፤ ከፑቲን እና ከክሬምሊን ጋር ቅርበት ያላቸውን አካላትን ዒላማ ማድረጉ እንቀጥልበታለን” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።