የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ “በሩሲያ የተያዘው መሬት ሳይመለስ የተኩስ አቁም የለም” አሉ
ዘሌንሰኪ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ ሞስኮ እንደገና እንድትታጠቅ እንደመፍቀድ ነውም ብለዋል
ፕሬዝዳንቱ ካለው ማዕበል አንጻር የምዕራባውያን የሮኬቶች አቅርቦቶች በቂ አይደሉም ሲሉም ተናግረዋል
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ በሩሲያ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ግዛቶች ሳይመልሱ የተኩስ አቁም ስምምነት የለም አሉ፡፡
ዘሌንስኪ አርብ ዕለት ከዎል ስትሪት ጆርናል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት ከሆነ የዩክሬን ግዛቶች በሩሲያ ኃይሎች ስር በሆኑበት የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ ጦርነቱን ማራዘም ነው ብለዋል፡፡
የተኩስ አቁም ስምምነቱ የበለጠ ግጭት እንዲባባስ የሚያደርግና ሞስኮ ለቀጣዩ ዙር እንደገና ለማስታጠቅ እድል እንድታገኝ የሚያደረግ መሆኑም አክለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
“ህብረተሰቡ ሁሉም ግዛቶች መጀመሪያ ነጻ መውጣት እንዳለባቸው ያምናል፣ ከዚያም በሚቀጥሉት መቶ ዘመናት ምን ማድረግ እና እንዴት መኖር እንዳለብን መስማማት እንችላለን”ም ነው ያሉት ዘሌንስኪ።
ዜለንስኪ አሜሪካ ለዩክሬን ስለሰጠቻቸው ከፍተኛ ተንቀሳቃሽነት ያላቸው ሮኬት አርቲለሪ ሲስተምስ (HIMARS) ሲናገሩም “የምዕራባውያን የሮኬቶች አቅርቦቶች ምንም እንኳን ጠቃሚ ቢሆኑም፤ ዩክሬን የተጋረጠባትን መዕበል ለመቀልበስ ከሚያስፈልጋት ድጋፍ አንጻር በጣም ያነሱ ናቸው” ብለዋል።
አሁን አንገብጋቢው ነገር የሩሲያ የረዥም ርቀት የሚከላከል የአየር መከላከያ ሲስተም ማግኘት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ዎል ስትሪት ጆርናል የዜለንስኪን አስተያየት በመጥቀስ “ከሩሲያ ፌዴሬሽን ጋር ያለውን ግጭት ማቀዝቀዝ ማለት የሩስያ ፌደሬሽን እስትንፋስ እንድታገኝ መፍቀድ እንደማለት ነው” ሲል ጽፏል።
ሩሲያ እና ዩክሬን የዩክሬን ጥቁር ባህር ወደቦች ለእህል መላክ ለመክፈት የሚያስችል አስደናቂ ስምምነት አርብ እለት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡ስምምነቱ በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የተባባሰውን ዓለም አቀፍ የምግብ ቀውስ ለማቃለል ተስፋ የፈጠረ ነው ተብሎለታል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የገለጹት ዩክክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ፤ ከሞስኮ ጋር የተፈረመው ዲፕሎማሲያዊ ስምምነት “ገበያውን በተወሰነ ደረጃ ሊያረጋጋ ይችላል ነገር ግን ጊዜያዊ እረፍት ብቻ የሚሰጥ ነው”ም ብለዋል።