የአውሮፓ ህብረት ከሩሲያ ጋር በተገናኘ በ19 የቻይና ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጣለ
ማዕቀብ የተጣለባቸው ኩባንያዎች የሳተላይት እና የተለያዩ የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂ የሚያመርቱ ናቸው
ህብረቱ በቀጣይ በተጨማሪ የሩሲያ ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ለመጣል እየተዘጋጀ መሆኑ ተሰምቷል
የአውሮፓ ህብረት የሩሲያን ጦርነት ደግፈዋል ባላቸው 19 የቻይና ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጣለ፡፡
ህብረቱ ኩባንያዎቹ ሩሲያ በዩክሬን ላይ እያደረገች ላለቸው ወታደራዊ ዘመቻ በጦር መሳራያ ቴክኖሎጂ እና ሳተላይት ሽያጭ ላይ ሲሳተፉ ደርሸባቸዋለሁ ብሏል፡፡
በሆንግ ኮንግ የሚንቀሳቀሱ ሁለት ኩባንያዎች እና አለም አቀፍ ግዙፍ የሳተላይት ኩባንያዎች ማዕቀቡ ከተጣለባቸው ተቋማት መካከል ይገኙበታል፡፡
ህብረቱ ከሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ጋር በተገናኝ ድጋፍ በማድረግ የሚወነጅላቸው አለምአቀፍ ተቋማት ቁጥር 675 ደርሷል፡፡
ኩባንያዎቹ የሞስኮን የመከላከያ እና የደህንነት ዘርፍ ለማጠናከር የሚውሉ ቴክኖሎጂዎችን መሸጥ የሚከለክለውን የአውሮፓ ህብረት መመሪያ መተላለፋቸው በመረጋገጡ ነው ማዕቀብ የተጣለባቸው ተብሏል፡፡
ባሳለፍነው ጥቅምት ወር አጃንስ ፍራንስ ፕረስ ባደረገው የምርመራ ዘገባ መቀመጫውን በቤጂንግ ያደረገ ዩንዝ የተባለ የሳተላይት ኩባንያ ከሩሲያው ወታደራዊ ቡድን ዋግነር ጋር የ30 ሚሊየን ዶላር የሳተላየት ሽያጭ ማድረጉን አጋልጦ ነበር፡፡
ሌላኛው በማዕቀቡ የተካተተው የቻይና የኤሮ ስፔስ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ለዋግነር እና ለሩሲያ የሳተላይት ምስሎችን በመሸጥ በህብረቱ ተወንጅሏል፡፡
ምንም እንኳን ቻይና እስካሁን ለሩሲያ በቀጥታ የጦር መሳርያ ድጋፍ ስለማድረጓ ባይረጋገጥም ለሞስኮ የጦር መሳሪያ ኢንዱስትሪዎች ግብአቶችን በመሸጥ አሜሪካ እና ምእራባዊያን በተደጋጋሚ ትወቀሳለች፡፡
ቤጂንግ ክሱን ከእውነት የራቀ ነው በሚል ብታስተባብለም ኩባንያዎቿን ከምዕራባዊያን ማእቀብ ማስጣል አልቻለችም፡፡
እስካሁን ድረስ 61 መቀመጫቸውን በሩሲያ ያደረጉ ኩባንያዎች 19 የቻይና ሁለት የቱርክ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ እና ህንድ አንድ ኩባንያ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል፡፡
14 ማዕቀፎች ያሉት ትላንት ይፋ የተደረገው የአውሮፓ ህብረት ማዕቀብ “ኤልኤንጂ” የተሰኝውን የሩሲያ የተፈጥሮ ነዳጅ አውጭ ኩባንያንም ማካተቱን ፍራንስ 24 አስነብብቧል፡፡ የነዳጅ ኩባንያው በድንበር አቋራጭ የነዳጅ ሽያጭ በአውሮፓ ሀገራት ወደቦች ለፊንላንድ ፣ ሲውዲን እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የሚያቀርበው የነዳጅ አቅርቦት ላይ ክልከላ ለማድረግም አቅዷል፡፡
በተጨማሪም ከሳይበር ደህንነት ጋር በተገናኘ በሩሲያ የሳይበር አሰሳ ስራ ላይ ተሳትፎ አላቸው የተባሉ 6 ግለሰቦች በማዕቀቡ ተካተዋል፤ ከነዚህ ግለሰቦች መካከል አራቱ ከሩሲያ የደህንነት ተቋማት ጋር ቀጥተኛ ግንኑነት እንዳላቸውም ነው ህብረቱ ያስታወቀው፡፡