የጦር መሳርያ ቴክኖሎጂ አምራቾች፣ የማዕድን አውጪዎችና የሩስያ ቱጃሮች በማዕቀቡ ከተካተቱት መካከል ይገኙበታል
የአሜሪካ ግምዣ ቤት እና እና የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መስርያ ቤት በሩስያ ላይ ያነጣጠረ አዲስ ማዕቀብ ይፋ አደረጉ፡፡
ማዕቀቡ በሩስያ ውስጥ እና ውጭ የሚገኙ 400 ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች ላይ አነጣጥሯል የተባለ ሲሆን የቻይና ኩባንያዎችም በማዕቀቡ ውስጥ መካተታቸውን ሲኤንኤን አስነብቧል፡፡
ከጦር መሳርያ ድጋፍ እና ምርት ጋር በተገናኝ ከሞስኮ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉት አካላት ምዕራባውያን በሀገሪቱ ላይ ከዚህ ከቀደም የጣሏቸው ማዕቀቦች የታቀደላቸውን ግብ እንዳይመቱ እክል ሆነዋል ነው የተባለው፡፡
የቻይና ኩባንያዎች በዚህ ወቀሳ ውስጥ በቅድሚያ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በአዲሱ ማዕቀብ ውስጥም የሩስያን የጦርነት ኢኮኖሚ በመደገፍ እና ለጦር መሳርያ ምርት የሚያገለግሉ እንደ “ማይክሮኤሌክትሮኒክ” እና “ማሽን ቱል” ያሉ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመሸጥ ማዕቀብ እንደሚጣልባቸው ተገልጿል፡፡
እነዚህ ኩባያዎች በቻይና እና በዚያው ሩስያ ፋብሪካዎችን ከፍተው በመስራት ላይ እንደሚገኙ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ይፋ ባደረገው ሰነድ ላይ አመላክቷል፡፡
ከዚህ ባለፈም ሞስኮ ከተለያዩ ሀገራት በምታስገባቸው ጦር መሳርያዎች፣ ተተኳሶች እንዲሁም ሌሎች ወታደራዊ ቁሳቁሶች ግዢን በማሳለጥ የሚሳተፉ ቱጃሮች በማዕቀቡ ውስጥ ከተካተቱት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
እነኚህ የሩስያ ቱጃሮች በውጭ ሀገራት ያላቸውን የባንክ ሂሳብ እና ግንኙነት በመጠቀም ወርቅን ወደ ገንዘብ በመቀየር ሞስኮ በምዕራባውያን ከዚህ ቀደም የተጣለባት ማዕቀብ ሳይገድባት በጦር መሳርያ ግዢ ላይ እንድትሳተፍ ተባብረዋል በሚል ወቀሳ ቀርቦባቸዋል፡፡
የብረት እና ሀይል አምራቾች፣ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች፣ የማዕድን አምራቾች እና ላኪዎች፣ የአውሮፕላን ሎጂስቲክ ኩባንያዎች ስማቸው በአዲሱ ማዕቀብ ውስጥ ከተካተቱ የሩስያ ተቋማት መካከል ይገኙበታል፡፡
ከማዕቀቡ በተጨማሪ ድሮን እና ሚሳኤሎች የተካተቱበት ለዩክሬን አዲስ የጦር መሳርያ ድጋፍ ማዕቀፍ አሜሪካ ይፋ አድርጋለች፡፡
የጦር መሳርያ ማዕቀፉን ይፋ ያደረጉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከዩክሬኑ አቻቸው ቮለደሚር ዘለንስኪ ጋር በትላንትናው እለት ባደረጉት የስልክ ውይይት “ለሁለት አመት ተኩል ያህል ሩስያ ለከፈትችው ፍትሀዊ ያልሆነ ጦርነት ዩክሬናውያን አለመንበርከካቸውን እናደንቃለን፤ ዩክሬን እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ነጻነቷን እና ሉአላዊነቷን አስጠበቃ ለመጓዝ የምታደርገውን ጉዞ እንደግፋለን” ብለዋል፡፡
በአዲሱ የጦር መሳርያ ድጋፍ ማዕቀፍ ውስጥ ጸረ ሚሳኤል ፣ የታንክ እና ሮኬት ተተኳሾች ፣ ድሮኖች እና ሚሳኤሎች መካተታቸው ነው የተነገረው፡፡