ሞስኮ ማዕቀቡን የጣለችው አሜሪካ ባሳለፍነው ሳምንት በሩሲያ ላይ ለጣለችው ማዕቀብ የአጸፋ እርምጃ ነው
ሩሲያ በ92 አሜሪካዊያን ላይ ማዕቀብ ጣለች።
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር እንዳስታወቀው በ92 አሜሪካዊያን ላይ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።
ማዕቀብ የተጣለባቸው አሜሪካዊያን ወደ ሩሲያ እንዳይገቡ፣ እንዳይሰሩ እና በሩሲያ ያላቸው ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ ታግደዋል።
ማዕቀብ ከተጣለባቸው አሜሪካዊያን መካከል የዎልስትሪት ጆርናል፣ ኒዮርክ ታየምስ፣ ዋሽንግተን ፖስት እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሚዲያዎች ውስጥ የሚሰሩ ጋዜጠኞች አሉበት።
ከጋዜጠኞች በተጨማሪም የህግ ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ታዋቂ የንግድ ሰዎች እና የሙያ ማህበራት አመራሮች ማዕቀቡ ተጥሎባቸዋል።
በአጠቃላይ ሩሲያ ወደ ግዛቷ እንዳይገቡ ማዕቀብ የጣለችባቸው አሜሪካዊያን ቁጥር ከ2 ሺህ እንዳለፈ ቪኦኤ ዘግቧል።
ባሳለፍነው ሳምንት አሜሪካ ከዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ በ400 ሩሲያ እና ቻይናዊያን ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።
ሩሲያም በአሜሪካ ለተጣለባት ማዕቀብ የአጸፋ እርምጃ የወሰደች ሲሆን ቻይና የዋሸንግተንን ማዕቀብ ከማውገዝ ባለፈ እስካሁን ተመሳሳይ ማዕቀብ ስለመጣሏ አልታወቀም።
ለአንድ ሳምንት በሚል የተጀመረው የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት ሶስተኛ ዓመቱ ላይ ይገኛል።
ይህ ጦርነት በድርድር እንዲያልቅ በተለያዩ አካላት ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም ጦርነት እንደቀጠለ ይገኛል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ሩሲያን ወደ ድርድር ለማምጣት በሚል በምዕራብ ሩሲያ በኩል በምትገኘው ኩርስክ ግዛት ጥቃት በመክፈት ቦታዎችን ተቆጣጥራለች።
ሩሲያ የዩክሬንን ጥቃት በምዕራባዊያን ሀገራት ድጋፍ የተደረገብኝ ነው በሚል ጉዳዩ ወደ ሶስተኛው የዓለም ጦርነት ሊያመራ ይችላል ስትል አስጠንቅቃለች።