የተመድ ሰብዓዊ እርዳታ ቢሮ “በሶማሊያ “ከፍተኛ የረሃብ አደጋ አንዣቧል” አለ
ማርቲን ግሪፊትስ፤ በሶማሊያ ከጥቅምት እስከ ታህሳስ ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ረሃብ ይከሰታል ሲሉም አስጠንቅቀዋል
በሶማሊያ ወደ 7 ነጥብ 1 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ለከፍተኛ የምግብ እጥረት መጋለጣቸው የተመድ ሪፖርት ያመላክታል
በአፍሪካ ቀንዷ ሀገር ሶማሊያ “ከፍተኛ የረሃብ አደጋ አንዣቧል” ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ሃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ ተናገሩ፡፡
ማርቲን ግሪፊትስ በሞቃዲሾ ተገኝተው በሰጡት መግለጫ ፤ በሶማሊያ ከጥቅምት እስከ ታህሳስ ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ረሃብ ሊከሰት ይችላል አስጠንቅቀዋል፡፡
በሀገሪቱ እየተባባሰ የመጣው ድርቅ ሁኔታ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ መናር በሀገሪቱ አስከፊ ረሃብ እንዲከሰት እያደረጉ ያሉ ምክንያቶች እንደሆኑ ኃላፊው መናገራቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
አሁን ላይ በሶማሊያ ወደ 7 ነጥብ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለከፍተኛ የምግብ እጥረት መጋለጣቸው የዓለም የምግብ ፕሮግራም ሪፖርት ያመላክታል፡፡
ከእነዚህ 1 ነየጥብ 5 ሚሊየን የሚሆኑት ከአምስት አመት በታች ያሉ ህጻናት ናቸው ተብሏል፡፡
ወደ 386 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ለከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጦት መጋለጣቸውንና በሞት አፋፍ ላይ መሆናቸውንም የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስታውቋል፡፡
ከዚህም በተጫመሪ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች መፈናቀላቸው ከእነዚህ ውስጥ 750 ሺህ የሚሆኑ በዚህ አመት ብቻ ሀገር ለቀው መውጣታቸው የዓለም የምግብ ፕሮግራም በቅርቡ ያካሄደው የዳሰሳ ጥናት አመላክቷል፡፡
በአፍሪካ ቀንድ ባለፉት 4 አስርት ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ መከሰቱን ተከትሎ ሶማሊያን ጨምሮ በርካታ የቀጠናው ሀገራት ዜጎች ለከፍተኛ ረሃብና ሞት መዳረጋቸውም ነው የተመድ ሪፖርቶች የሚያመላክቱት፡፡
በተከሰተው ረሃብ በተለይም ሴቶችና ህጻናት የበለጠ ጉዳት በማስተናገድ ላይ መሆናቸውንም የተመድ ቃል አቀባይ ፋርሃን ሀቅ በቅረቡ በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡
በተለይም አልሻባብ በተቆጣጠራቸው የተወሰኑ የደቡብ እና ማዕከላዊ ሶማሊያን አካባቢዎች ያለው ሁኔታ እጅግ አስከፊና በርካቶች ህይወታቸው እያጡ ያሉበት መሆኑ ይገለጻል፡፡
ሌላው ምክንያት ደግሞ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ የሰጠው እጅግ የዘገየ ምላሽ ሲሆን አሁንም የአደጋ ደወሉ በድጋሚ እያስተጋባ ነው።