ስምንት ሰዓት ይወስድ የነበረውን በረራ ወደ 110 ደቂቃ ዝቅ የሚያደርግ የሀይድሮጅን ጄት ተሰራ
ዴስቲነስ የተሰኘ የምህንድስና ኩባንያ አዲስ የሀይድሮጅን ጄት መስራቱን አስታውቋል
ይህ አዲስ የመንገደኞች አውሮፕላን ከድምጽ አምስት እጥፍ ይፈጥናል ተብሏል
የፈረንሳይ መዲና ከሰሞኑ በርከት ያሉ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን አስተናግዳለች ።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድን (ዶ/ር) ጨምሮ የዓለም ሀገራት የተሳተፉበት የዓለም ፋይናንስ ጉባኤ አንዱ ሲሆን ሌላኛው መድረክ ደግሞ የዓለም አቪዬሽን ቴክኖሎጂ ወይም ኤርሾው ነው።
በዚህ ሁነት ላይ የዓለም አቪዬሽን ቴክኖሎጂ አዳዲስ ፈጠራዎች ለእይታ የቀረበ ሲሆን የብዙ ጎብኚዎችን ትኩረት የሳበው የሀይድሮጅን ሀይፐርሶኒክ አውሮፕላን ዋነኛው እንደነበር ተገልጿል።
- የሩሲያው “Su-25” የጦር ጄት ከአሜሪካው “A-10” የጦር ጄት ጋር ሲነጻፀሩ
- ሚሳዔልና ተተኳሽ ቦምቦችን ጭኖ በሰዓት ከ2 ሺህ ኪ.ሜ በላይ የሚበረው “ሚኮያን ሚግ-35” ጄት
ዋና መቀመጫውን ስዊዝ ያደረገው ዴስቲነስ የተሰኘው ኩባንያ ላለፉት ሁለት ዓመታት የሙከራ በረራውን ሲያካሂድ እንደቆየ ተናግሯል።
ይህ ኩባንያ ከፓሪስ-ኒዮርክ የሙከራ በረራ ያካሄደ ሲሆን ከዚህ በፊት ስምንት ሰዓት ይፈጅ የነበረውን በረራ ወደ አንድ ሰዓት ከግማሽ ዝቅ እንዲል ማድረጉን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።
ፍጥነቱ ከድምጽ አምስት እጥፍ ይቀድማል ወይም በሰዓት ከስድስት ሺህ በላይ ኪሎ ሜትር ይጓዛል የተባለው ይህ ሀይፐር ሶኒክ አውሮፕላን በሀይድሮጅን የሚሰራ የመጀመሪያው አውሮፕላን ነው ተብሏል።
ኩባንያው የስፔን መንግስት ያወጣውን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድር በማሸነፍ 12 ሚሊዮን ዩሮ መሸለሙ በገንዘብ በኩል ያለ ገደብ የሙከራ ስራውን እንዲያሳካ እንዳገዘው አስታውቋል።
በዓለማችን በፍጥነት ቀዳሚ የሆነው ኮንኮርድ የተሰኘው የአንግሎ-ፍሬንች ኩባንያ ክብረወሰን ያለው ሲሆን ከፓሪስ-ኒዮርክ ያለውን ርቀት በሶስት ሰዓት ከ50 ደቂቃ ውስጥ ተጉዟል።
ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ ከፓሪስ-ኒዮርክ ያለውን ርቀት በ90 ደቂቃ ውስጥ እንደሚጨርሱ ይጠበቃል ተብሏል።
ከአውስትራሊያ-ጀርመን ፍራንክፈርት ለመብረር አሁን ላይ 20 ሰዓት የሚፈጅ ሲሆን በአዲሱ ቴክኖሎጂ ግን ወደ አራት ሰዓት ዝቅ እንደሚል ይጠበቃል።
ቦይንግ እና ሌሎች የዓለማችን የአቪዬሽን ኩባንያዎች የበረራ ቴክኖሎጂ የሀይል ምንጮችን ከነዳጅ ወደ ታዳሽ ሀይል ለመቀየር ጥናቶችን በማድረግ ላይ ናቸው።
የሀይል ምንጫቸው ታዳሽ ሀይል የሆኑ የአቪዬሽን ምርቶች የቀጣዮቹ ዘመናት ዋነኛ ምርጫ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።