“በሽታን የመፍራት አባዜ” ከልብና ደም ቧንቧ ህመም በላይ ገዳይ ነው - ጥናት
በስዊድን ተመራማሪዎች የተደረገ ጥናት ስለጤናቸው አብዝተው የሚጨነቁና በሽታን አጥብቀው የሚፈሩ ሰዎች እድሜያቸውን እያሳጠሩ ነው ብሏል
የዚህ ችግር ተጠቂዎች ሳይታመሙ ሆስፒታል የሚመላለሱና ያላጠቃቸውን በሽታ የሚያስታምሙ ናቸው
በቅርቡ የተደረገ ጥናት ስለጤናቸው አብዝተው የሚጨነቁ ሰዎች እድሜያቸውን ያሳጥራሉ ብሏል።
የስዊድን ተመራማሪዎች “በሽታ የመፍራት አባዜ” ያለባቸው ሰዎች ላይ ጥናት አድርገዋል።
በህክምናው “ኢልነስ አንዛይቲ ዲስኦርደር” የሚል ስያሜ ያለው ችግር ከተለያዩ ህመሞች አንጻር ገዳይነቱ ከሚታሰበው በላይ መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል።
የዚህ ችግር ተጠቂዎች ስለጤናቸው ከልክ በላይ ይጨነቃሉ፤ ምንም በሽታ ሳይኖርባቸውም እንደታመሙ ያስባሉ። በዚህም ምክንያት ምንም ነገር ሳይገጥማቸው ወደ ህክምና ተቋማት በተደጋጋሚ ይመላለሳሉ።
አንዳንዶቹም “ገዳይ በሽታ” እንዳጠቃቸው በባለሙያዎች ይነገረናል በሚል ፍራቻ ወደ ሀኪም ቤት ከመሄድ ቤታቸው ውስጥ ያልያዛቸውን በሽታ ማስታመም ይመርጣሉ።
የፍርሃታቸው አንደኛው መንስኤ ወላጆቻቸውና የቅርብ ቤተሰቦቻቸውን ያጠቃ ከባድ ህመም በዘር ወደኛ ይተላለፋል የሚል ነው።
በዚህ ችግር የሚንገላቱ 1 ሺህ ሰዎችን ጨምሮ በ42 ሰዎች ላይ ለ20 አመታት የተደረገው ጥናትም ስለጤናቸው አብዝተው የሚጨነቁና የህመም ፍርሃት ያለባቸው ሰዎች ራሳቸውን ይበልጥ እየጎዱ እንደሚገኙ ነው ያመላከተው።
ጥናቱ በሽታን የሚሸሹና የሚፈሩት፤ ህመም ሳይጎበኛቸው ጭንቀታቸው ብቻ አካላዊና አዕምሯዊ ጤናቸውን የሚያዛባባቸው ሰዎች በልብ፣ በደም ቧንቧና መተንፈሻ አካላት በሽታዎች ምክንያት ከሚደርስ ሞት በበለጠ ለህልፈት የመዳረግ እድላቸው ከፍ ያለ መሆኑንም አሳይቷል።
በዚህ “ህመም የመፍራት አባዜ” ውስጥ ያሉ ሰዎች ለከፍተኛ ድብርትና ፍርሃት ስለሚጋለጡ ራሳቸውን እንደሚያጠፉም ተገልጿል።
በዚህ ህመምን ይዞኛል ወይም ሊይዘኝ ነው በሚል ከባድ ጭንቀት የሚሰቃዩ ሰዎች ለሌሎች በሽታዎች ተጋላጭ የመሆናቸውና የመሞት ምጣኔያቸውም ጭንቀት ከሌለባቸው ሰዎች እጅግ ከፍ ያለ መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል።
የስዊድን ተመራማሪዎች ያደረጉት ጥናት በዚህ ችግር ውስጥ ያሉ ሰዎች ያለ እድሜያቸው የመሞት እድላቸው 84 በመቶ መሆኑንና ችግሩ ከሌለባቸው ሰዎች ከአምስት አመት በፊት ቀድመው እንደሚሞቱ ማሳየቱንም የዋሽንግተን ፖስት ዘገባ ያሳያል።