አሰልጣኝ ቴን ሃግ “ዴቪድ ዴ ሂያ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር እንደሚቆይ ተስፋ አደረግላሁ” አሉ
ዩናይትድ የስፔናዊውን ግብ ጠባቂ ኮንትራት ለማራዘም እርግጠኛ እንዳልሆነ እየተነገረ ነው
ኤሪክ ቴን ሃግ፤ “ብዙ ጊዜ እንደገለጽኩት በዴቪድ ዴ ሂያ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ እሱ ምርጥ ግብ ጠባቂ ነው” ብለዋል
የማንቸስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ዩናይትድ ዌስትሃምን 1ለ0 ባሸነፉበት ጨዋታ ድንቅ ብቃት ያሳውን ግብ ጠባቂ ዴቪድ ዴ ሂያ በክለቡ እንደሚቆይ ያላቸውን ተስፋ ገለጹ።
ዴ ሂያ በሁለተኛው አጋማሽ ሶስት አስደናቂ የግብ ሙከራዎችን በማዳን ስምንት ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ እያንሰራራ ያለውን ክለብ በፕሪምየር ሊጉ ወደ 5ኛ ደረጃ ከፍ እንዲል የበኩሉን ሚና የተጫወተ ነው፡፡
ይሁን እንጅ ዩናይትድ በቅርቡ ውሉን የሚያልቀው የስፔናዊውን ግብ ጠባቂ ኮንትራት ለማራዘም እርግጠኛ እንዳልሆነ የእንግሊዝ ሚዲያዎች በመዘገብ ላይ ናቸው፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የክለቡ አሰልጣኝ ቴን ሃግ" አሁን ትኩረታችን በጨዋታዎቹ ላይ ነው፡፡ ቀጣይ የዓለም ዋንጫ አለ፤ ስለ ኮንትራቶች ጉዳይ ከዛ በኋላ ማሰብ እንችላለን " ብለዋል፡፡
“ብዙ ጊዜ እንደገለጽኩት በዴቪድ ዴ ሂያ በጣም ደስተኛ ነኝ እሱ ምርጥ ግብ ጠባቂ ነው” ያሉት ቴን ሃግ፤ ግብ ጠባቂው ከዩናይትድ ጋር ይቆያል የሚል ተስፋ አለኝ ማለታቸው ስካይ ስፖርት ዘግቧል፡፡
“ገና 31 አመቱ ነው፤ የበለጠ ብቃት ማሳየት ይችላል፤ ቀድሞውንም ለማንቸስተር ዩናይትድ በሚያስደንቅ ሁኔታ ጥሩ ነበር እናም ወደፊትም ተመሳሳይ ብቃት እንደሚያሳይ አስባለሁ” ነው ያሉት ቴን ሃግ፡፡
ዴቪድ ዴ ሂያ እና ሎሎች ነባርና አዳዲስ ተጨዋቾች የያዘው ማንቸስተር ዩናይትድ እያሳየ ባለው ብቃት በ2022/2023 የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን ተፎካካሪ ክልቦች አንዱ ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
በተለይም ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች ያሳየው የአሸናፊነት ብቃት የእግር ኳስ አፍቃሪያን አጀማመራቸው ጥሩ ባልነበረው ቴን ሃግ ላይ በድጋሚ ተስፋ እንዲያደርጉ ያስቻለ ነው ተብሏል፡፡
ስፔናዊው የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ በቅርቡ በሰጡት አስተያየት “ኤሪክ ቴን ሃግ ዩናይትዶችን ወደ ቀድሞ ብቃታቸው እየመለሳቸው ለመሆኑ ምልክቶች አሉ" ማለታቸው አይዘነጋም፡፡
ፔፕ ጋርዲዮላ ዩናይትድ በቴን ሀግ መሪነት ጠንካራ ፐሪምየር ሊጉ ተፊካካሪ ክለብ ሆኖ እንደሚመጣ ያላቸው እምነትም ገልጸዋል፡፡
"ዩናይትድ ተመልሶ እንደሚመጣ ይሰማኛል፤ በመጨረሻም ዩናይትድ ተመልሶ ይመጣል"ም ነበር ያሉት ጋርዲዮላ፡፡