የ39 ዓመቱ ዝላታን ኢብራሂሞቪች ለብሔራዊ ቡድን ተጠራ
በክለብ ለኤሲሚላን የሚጫወተው ኢብራ በ62 ጎሎች የብሔራዊ ቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች ነው
አንጋፋው አጥቂ ከብሔራዊ ቡድን ራሱን ካገለለ ከ 5 ዓመት በኋላ ነው ዳግም ወደ ቡድኑ የተመለሰው
ዝላታን ኢብራሂሞቪች ለ2022 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የስዊድን ብሔራዊ ቡድንን እንዲቀላቀል ጥሪ ተደርጎለታል፡፡ አሁን ላይ ለጣሊያኑ ኤሲ ሚላን በመጫወት ላይ የሚገኘው የ39 ዓመቱ ስዊድናዊ ፣ ሀገሩ ከዩሮ 2016 መሰናበቷን ተከትሎ ከብሔራዊ ቡድኑ በፈቃዱ ጡረታ ወጥቶ ነበር፡፡
ከ5 ዓመታት የጡረታ ቆይታ በኋላ የተመለሰው አንጋፋው አጥቂ ወደ ብሔራዊ ቡድኑ መመለሱን በትዊተር ገጹ ይፋ አድርጓል፡፡
ጎል እንደዘገበው ተጫዋቹ ለኳታሩ የ2020 የዓለም ዋንጫ ሀገሩ የምታደርገውን ጉዞ ለማቅናት በዚህ ወር ከጆርጂያ እና ኮሶቮ ጋር ለሚያደርጉት ግጥሚያ በጄን አንደርሰን ስብስብ ውስጥ ተካቷል፡፡
ኢብራሂሞቪች ለቡድኑ ምን አስተዋጽኦ ይኖረዋል በሚል ለብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ፣ “በመጀመሪያ ደረጃ እርሱ በጣም ምርጥ የእግርኳስ ተጫዋች ነው፡፡ ለመመለስ በመወሰኑ ደስተኛ ነኝ፡፡ በሜዳ ላይ ከሚኖረው ሚና በተጨማሪ የማይታመን ልምድ ያለው በመሆኑ ለቡድኑ ተጫዋቾች ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል” ብለዋል፡፡
ኢብራሂሞቪች ለስዊድን የመጀመሪያውን ጨዋታ እ.ኤ.አ. በ 2001 ያደረገ ሲሆን በእስካሁን ቆይታውም በሁለት የዓለም ዋንጫዎች እና በአራት የአውሮፓ ሻምፒዮናዎች ላይ የተሰለፈባቸውን ጨምሮ ለሀገሩ 116 ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ ኢብራ በ62 ጎሎች የብሔራዊ ቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋችም ነው፡፡
በዚህ የውድድር ዓመት በሴሪ አ ለኤሲሚላን ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች 14 ጎሎችን ማስቆጠር የቻለው ዝነኛው አጥቂ ፣ በብሔራዊ ቡድኑም ድንቅ ተሰጥኦውን ሊያሳይ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡