አይሲሲ በቀድሞው የሱዳን ፕሬዘዳንት አልበሽር ተላልፎ መሰጠት ዙሪያ የመጀመሪያውን አስተያየት ሰጠ
አይሲሲ በቀድሞው የሱዳን ፕሬዘዳንት አልበሽር ተላልፎ መሰጠት ዙሪያ የመጀመሪያውን አስተያየት ሰጠ
ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር ተላልፈው ሊሰጡ ነው ከተባለ በኋላ የመጀመሪያውን አስተያየት ሰጠ፡፡
ተቋሙ እስካሁን መደበኛ በሆነ መልኩ የቀድሞው የሱዳን መሪ በፍርድ ቤቱ ይዳኛሉ የሚል ማረጋገጫ እንዳልደረሰው ይፋ አድርጓል፡፡የአይሲሲ ቃል አቀባይ ፋዲ አል አብዱላህ ከሱዳን ምንም የደረሰን መደበኛ ማረጋገጫ እስከሌለ ድረስ በአልበሽር ተላልፎ መሰጠት ዙሪያ የምንለው ነገር የለም ብለዋል፡፡
የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት በአንድ ወቅት በደቡብ አፍሪካ በስብሰባ ላይ ሳሉ ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተላልፈው ሊሰጡ የነበረ ቢሆንም በብዙ ሃገራት ትብብር ሳይሳካ መቅረቱ ይታወሳል፡፡ አሁን ላይ ግን የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ኦማር ሃሰን አልበሽር ከሃገር ውጭ እንዲዳኙ ወስኗል፡፡
በርካቶች ታዲያ ይህንን ውሳኔ ሲቃወሙት እንደነበር ይታወሳል፡፡
ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የፖለቲካ ፍርድ ቤት እንጅ ትክክለኛ የፍትህ ተቋም አይደለም በሚልም መሪዎቹ ሳይቀሩ ሲናገሩት ቆይተዋል፡፡የአልበሽር ጠበቃም የቀድሞው የሱዳን መሪን ጉዳይ የሀገሪቱ ፍርድ ቤት መዳኘት ይችላልም የሚል ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡
ጠበቃው መሐመድ አል ሃሰን አል አሚን የደንበኛዬ (አልበሽር) ጉዳይ ወደ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት መሄድ የለበትም ሲሉም የሽግግር መንግስቱን ውሳኔ ተቃውመዋል፡፡
የሱዳን የፍትህ ተቋማት የአልበሽርን ጉዳይ ለመዳኘት አያንሱም ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
በ33ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ሲካሄድ የአህጉሩ መሪዎች የአፍሪካን ችግር የሚፈታው አፍሪካዊ መፍትሄ ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ይሁንና ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በወንጀል የሚጠረጠሩ ሰዎች ከአፍሪካ ውጭ እንዲዳኙ ይፈልጋል፣ጫናም ያደርጋል የሚል ወቀሳ ይሰነዘርበታል፡፡
ወንጀል የሰሩ ሰዎች በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት መዳኘት አለባቸው የሚሉት ደግሞ በአፍሪካ በህዝብ ታአማኒ የሆነ የፍትህ ተቋም ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ጥሩ አማራጭ ነው፣አምባገነኖች የፍትህ ተቋሞችን በማዳከም ጭምር እጃቸው ስላለበት በአፍሪካ መዳኘቱ በህዝብ ላይ መቀለድ ነው የሚል ሃሳብን መከራከሪያ አድርገው ያነሳሉ፡፡
ያም ሆነ ይህ ሱዳን የቀድሞ መሪዋን ፍርድ የምትከታተለው እንጅ የምትፈጽመው እንዳልሆነ አስታውቃለች፡፡