ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት (አይሲሲ) “በዳርፉር ጉዳይ” የምስክርነት ቃል መስማት ጀመረ
ዓሊ ኩሻብ ባለፈው ዓመት ችሎት ክሱ “ከእውነት የራቀ ነው” ማለታቸው የሚታወስ ነው
ፍርድ ቤቱ በጃንጃዌድ ሚሊሻ መሪው “አሊ ኩሻብ” ላይ ነው የምስክርነት ቃል በማዳመጥ ላይ የሚገኘው
ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ/አይሲሲ/ በዳርፉር ተፈፀመ ስለተባለው የግድያ ፣ አስገድዶ መድፈር እና ማሰቃየት ወንጀል የምስክርነት ቃል መስማት ጀመረ፡፡
የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዓቃቤ ህግ እ.ኤ.አ ከ2003 እስከ 2004 በሱዳን የተቀሰቀሰውን አስከፊ ግጭት ተከትሎ ለደረሰው ጭፍጨፋ “መሪ ተዋናይ ነበር ባለው የጃንጃዌድ ሚሊሻ መሪ አሊ ኩሻብ” ላይ የምስክርነት ቃል መስማት መጀመሩን የፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ፋቱ ቤንሱዳ አስታውቀዋል፡፡
“በዳርፉር ጉዳይ ከተጠረጠሩት መካከል አንዱ የሆነው ግለሰብ በገለልተኛ ፍርድ ቤት ፊት ቀርቦ ማየት መቻሌ ትልቅ እድል ነው ፤ በዳርፉር ግጭት የተጎዱና ሰለባ የሆኑ ተጠቂዎች ይህ የፍትህ ቀን እንዲመጣ እስካሁን ላሳዩት ትዕግስትና ፅናትም ያለኝን ትልቅ አድናቆት ለመግለፅ እወዳለሁ” ብለዋል ዓቃቤ ሕግ ፋቱ ቤንሱዳ፡፡
ዓሊ መሀመድ ዓሊ አብዱል ራህማን /ዓሊ ኩሻብ/ በዳርፉር ተፈፀመ በተባለው የግድያ፣ አስገድዶ መድፍርና ማሰቃየትን በመሳሰሉ በሰብአዊነት ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎችና የጦር ወንጀል 31 ክሶች እንደተመሰረቱበት የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ ያመለክታል፡፡
ዓሊ ኩሻብ ባለፈው ዓመት በነበረው ችሎት ክሱ “ከእውነት የራቀ ነው” ሲሉ ለዳኞች መግለፃቸው የሚታወስ ነው፡፡
የዛሬው ችሎት ዋና ዓላማ በኩሻብ ላይ የሚሰሙ የምስክርነት ቃሎች በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ለፍርድ ለመቅረብ የሚያስችሉ ጠንካራ ማስረጃዎች ናቸው ወይስ አይደሉም የሚለውን ለማረጋገጥ ነው ተብሏል፡፡
የዚህ ችሎት ውሳኔ በዚህ ዓመት መጨረሻ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ የዓሊ ኩሻብ ጠበቃ ሲረል ላውቺ በፍርድ ቤቱ እንደሚከራከሩም እንዲሁ፡፡