በሱዳን ምዕራብ ዳርፉር ለ137 ሰዎች ሞት ምክንያት በሆነው ግጭት ዙሪያ ምርመራ እነዲደረግ ተመድ አስጠነቀቀ
በግዛቱ ዋና ከተማ ያለው የተኩስ ልውውጥ አሁን ላይ ጋብ ማለቱ ተገልጿል
በግጭቱ ከተሳተፉ ሚሊሻዎች ውስጥ የተወሰኑት ዳርፉርን ከሚያዋስኑ ጎረቤት ሀገራት የገቡ መሆናቸው ተገልጿል
በሱዳን የምዕራብ ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ አል-ጂኔይና በማሳላሊት እና አረብ ጎሳዎች መካከል በተከሰተ የጎሳ ግጭት 137 ሰዎች መሞታቸውን የመንግስታቱ ድርጅት ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ቃል አቀባይ ማርታ ሀደሮ ተናግረዋል።
በግጭቱ ህይወታቸው ካለፈ 137 ሰዎች በተጨማሪ በ221 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተገልጿል። በከተማዋ የሚኖሩ ከ700 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በግጭቱ እንቅስቃሴያቸው ታውኮ ቆይቷል።
በዚህም ምክንያት የሱዳን መንግስት ከግጭቱ ለተረፉ ሰዎች ጥበቃ እነዲያደርግ እና ምርመራ እንዲደረግ የመንግስታቱ ድርጅት አስጠንቅቋል።
የዐይን እማኞች ለአል ዐይን ዜና እንደገለጹት፣ በአከባቢው ቤቶችን ማቃጠልን ጨምሮ በሁለት ጎሳዎች መካከል በሚደረጉ የተኩስ ልውውጦች ከተማዋ ከባድ የፀጥታ ሁኔታ ውስጥ ቆይታለች።
እንደ እማኞች ገለፃ የችግሩ መንስዔ በአል-ጃባል አካባቢ አንድ የጎሳ ቡድን ሁለት የማሳሊት ጎሳ ተወላጆችን መግደሉ ነው።
የተጎጂዎች ቤተሰቦች እሁድ ዕለት ተሰብስበው ባለሥልጣናት ወንጀለኞቹን በቁጥጥር ስር እንዲያውሉ ቢጠይቁም ይህ ሊሆን አልቻለም ነው የተባለው።
ሌላ ቡድን ደግሞ በተጎጂዎች የቀብር ሥነ ስርዓት ላይ ጥቃት በመፈፀም ሦስተኛ ሰው መግደሉ ሁኔታውን ይበልጥ ማባባሱን እማኞች ገልጸዋል፡፡
ግጭቶች በተከሰቱበት አል-ጂኔይና ከተማ የአል-ጃባል አካባቢ በርካታ ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን “በአቡዛር የተፈናቃዮች ካምፕ የሚገኙ ቤቶች እና በአካባቢው የሚገኝ የህክምና ማዕከል ተቃጥለዋል” ብለዋል ምስክሮች።
የምዕራብ ዳርፉር አስተዳዳሪ መሃመድ አብደላህ በትናትናው እለት በሰጡት መግለጫ አሁን ላይ አካባቢው መረጋጋቱን እና በሚሊሻዎች መካካል ስደረግ የነበረው የተኩስ ልውውጥ ጋብ ማለቱን አስታውቀዋል። በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት ካደረሱ ሚሊሻዎች ውስጥ የተወሰኑት ዳርፉርን ከሚያዋስኑ ጎረቤት ሀገራት የገቡ መሆናቸውን አስተዳዳሪው አንስተዋል።