በፑቲን እና ኔታንያሁ ላይ የእስር ማዘዣ እንዲወጣ የጠየቁት የአይሲሲ አቃቤህግ በወሲባዊ ትንኮሳ ምርመራ ተጀመረባቸው
የአለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ካሪም ካን በጾታዊ ትንኮሳ የውስጥ ምርመራ እየተደረገባቸው ነው
ዋና አቃቤ ህጉ ምርመራው እስኪጠናቀቅ ድረስ ከሃላፊነት ሊነሱ እንደሚችል ተነግሯል
በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ የጦር ወንጀል ክስ እንዲመሰረት የጠየቁት የአለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና አቃቤ ህግ ካሪም ካን በፆታዊ ጥቃት ምርመራ ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል።
ጉዳዩ የተሰማው በግንቦት ወር ሲሆን ዋና አቃቤ ህጉ በኔታንያሁ እና በተሰናባቹ የመከላከያ ሚንስትር ዮአቭ ጋላንት ላይ የእስር ማዘዣ ከመጠየቃቸው ከጥቂት ሳምንታት በፊት ነበር።
የአይሲሲ ዳኞች በአሁኑ ወቅት አቃቤ ህጉ በግንቦት ወር በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በመከላከያ ሚንስትሩ እና በሃማስ መሪዎች ላይ የእስር ማዘዣ ኢንዲወጣ ያቀረቡትን ጥያቄ እየገመገሙ ነው።
ካን የጥፋተኝነት ውንጀላው በጽህፈት ቤታቸው ላይ እየተካሄደ ከሚገኘው የተሳሳተ መረጃ ዘመቻ ጋር የተገናኘ ነው ሲሉ አስተባብለዋል።
ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ሪፖርት ያደረጉት ሁለት ሴቶች ለድርጅቱ የውስጥ ምርመራ ክፍል ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን አጣሪ ቡድኑ ተፈጽሟል የተባለውን ትንኮሳ ለውጭ የህግ አካላት አሳልፎ ከመስጠቱ በፊት ማጣርያዎችን እያደረገ ነው ተብሏል፡፡
በውንጀላው ዙርያ ለውይይት የተሰራጨው የውስጥ ሰነድ የሥነ ምግባር ጉዳዮችን የሚመረምረው የፍርድ ቤቱ ገለልተኛ አካል ክሱ መጀመሪያ ላይ በቀረበበት ወቅት መደበኛ ምርመራ ማድረግ ነበረበት ሲል ተከራክሯል።
የጾታዊ ጥቃት ክሶቹ ባለፈው ወር በፍርድ ቤቱ የበላይ አካል ምርመራ እንዲደረግባቸው ትዕዛዝ ከተሰጠ በኋላ ድርጊቱን ፈጽመዋል የተባሉት የፍርድ ቤቱ ዋና አቃቤ ህግ ካን ድርጊቱን እንዳልፈጸሙ በመግለጽ ምርመራው እንዲቋረጥ ጠይቀዋል፡፡
በዚህ ሳምንት ለድርጅቱ አባል ሀገራት የተላከው ደብዳቤ ምርመራው እስከሚጠናቀቅ ድረስ አቃቤ ህጉ በጊዜያዊነት ከሀላፊነታቸው ሊነሱ እንደሚችሉ ማመላከቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የስነ ምግባር ጉዳዮችን የሚያጣራው የህግ አካል የሚመሩት ሃላፊ በዋና አቃቤህጉ ቢሮ ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ በመሆናቸው ተበዳዮቹ በውስጥ ምርመራው ላይ እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡
በዚህም አጣሪ ኮሚቴው በእጁ ላይ የሚገኙትን መረጃዎች ለኔዘርላንድ መደበኛ የፍትህ ሰዎች በማስተላለፍ ጉዳዩ ማጣርያ እንዲደረግበት ጠይቀዋል፡፡