ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ላይ የእስር ማዘዣ ሊያወጣ መሆኑ ተገለጸ
የእስር ማዘዣው በጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ እና የሀማሱ መሪ እና ከስር ባሉ አመራሮች ላይ ይሆናል ተብሏል
እስራኤል ፍርድ ቤቱ የእስር ማዘዣ ሊያወጣ እንደሚችል እና ይህ እንዳይሆን የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገች እንደሆነ ተገልጿል
ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በእስራኤል ከፍተኛ አመራሮች ላይ የእስር ማዘዣ ሊያወጣ እንደሚችል ተገለጸ።
ለፍልስጤማዊያን ነጻነት እንደሚታገል የሚገልጸው ሀማስ ባሳለፍነው ጥቅምት በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ነበር በአካባቢው ጦርነት የተቀሰቀሰው።
በዚህ ጦርነት ምክንያት ከ34 ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያን እና 1 ሺህ 200 እስራኤላዊያን ተገድለዋል።
እስራኤል ለደረሰባት ጥቃት የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ እና በሀማስ የታገቱ ዜጎችን ለማስለቀቅ የአየር ላይ እና ምድር ላይ ጥቃቶችን በመፈጸም ላይ ትገኛለች።
እስራኤል በጋዛ እና ሌሎች የፍልስጤም አካባቢዎች ላይ በወሰደቻቸው ጥቃቶች ህጻናት እና ሴቶች ለከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጋልጠዋል በሚል ክሶች እና ወቀሳዎች ቀርበውባታል።
የእስራኤል ጦርም ለተጎጂዎች የህይወት አድን እርዳታዎች እንዳይገቡ አድርጓል፣ ጦሩም የጦር ወንጅል ፈጽሟል የሚሉ ክሶች በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት ቀርቦበታል።
እንዲሁም የሀማስ መሪዎች ንጹሀን ዜጎችን በማገት እና በማሰቃየት ተመሳሳይ የጦር ወንጀል እንደቀረበበት ኒዮርክ ታይምስ ዘግባል።
በዚህ ምክንያትም ፍርድ ቤቱ በእስራኤል እና ሀማስ መሪዎች ላይ የእስር ማዘዣ ለማውጣት ጫፍ ላይ እንደደረሰ ዘገባው አመልክቷል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በቀጥታ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤቱን ስም ባይጠቅሱም እስራኤል ራሷን ለመከላከል የትኛውንም እርምጃ ከመውስድ የሚያስቆማት አካል የለም ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
እስራኤል በ126 ፈራሚ ሀገራት የተቋቋመው ዓለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት አባል ባትሆንም በጠቅላይ ሚንስትሯ እና ጦር አመራሮቿ ላይ የእስር ማዘዣ ሊወጣባቸው እንደሚችል በማሰብ ይህ እንዳይሆን በእንቅስቃሴ ላይ መሆኗ ተገልጿል።
ሰባተኛ ወሩን ሊደፍን ጥቂት ቀናት የቀሩት የእስራኤል-ሀማስ ጦርነት በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶችን እያስተናገደ የቀጠለ ሲሆን የተኩስ ማቆም ስምምነት ለማድረግ በቃል ደረጃ ስምምነት የተደረሰ ቢሆንም እስካሁን በይፋ ጦርነቱ አልቆመም።
ደቡብ አፍሪክ፣ ቱርክ እና ሌሎችም በርካታ የዓለማችን ሀገራት እስራኤል በፍልስጤማዊያን ላይ የጦር ወንጀል ፈጽማለች በሚል በይፋ የተናገሩ ሀገራት ናቸው።
እስራኤል እያደረኩት ያለው ጦርነት ራሴን ለመከላከል ነው ብትልም እንደ ቻይና እና መሰል ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገራት ደግሞ እስራኤል በሀማስ ስም ፍልስጤማዊያንን ለማጥፋት የተጋነነ እርምጃ ወስዳለች ብለዋል።