ደቡብ አፍሪካ የአለማቀፉ ፍርድቤት እስራኤል ከራፋህ እንድትወጣ እንዲያዝ ጠየቀች
አሜሪካም ወደ እስራኤል የላከቻቸው የጦር መሳሪያዎች አለማቀፍ ህግን በጣሰ መንገድ ጥቅም ላይ መዋላቸውን አምናለች
አለማቀፍ ጫናው የበረታባቸው ኔታንያሁ ግን “በጥፍራችንም ቢሆን እንዋጋለን እንጂ ወደኋላ አንመለስም” እያሉ ነው
ደቡብ አፍሪካ የአለማቀፉ ፍርድቤት (አይሲጄ) እስራኤል ከራፋህ ለቃ እንድትወጣ እንዲያዝ መጠየቋ ተሰማ።
እስራኤል በጋዛ የዘር ፍጅት ፈጭማለች በሚል ክስ ያቀረበችው ፕሪቶሪያ በቴል አቪቭ ላይ አስቸኳይ ውሳኔ እንዲተላለፍ የሚጠይቅ ክስ ማቅረቧን ፍርድቤቱ አስታውቋል።
“የፍልስጤማውያን የመጨረሻ መሸሸጊያ ናት” ባለቻት ራፋህ ላይ እስራኤል ለመጀመር ያሰበችውን የምድር ውጊያ እቅድ እንድትሰርዝም ፍርድቤቱ ውሳኔ ያሳልፍ ዘንድ ጠይቃለች ነው የተባለው።
የመንግስታቱ ድርጅት ሃላፊዎች፣ አለማቀፍ ተቋማት፣ ጋዜጠኞችና መርማሪዎች ወደ ራፋህ ገብተው ያለውን ሁኔታ እንዲመለከቱና ያልተገደበ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲገባ ማድረግ እንደሚገባም በመጥቀስ።
ደቡብ አፍሪካ የእስራኤል ጦር በጋዛ ፍልስጤማውያንን አንድም በጦርነት አልያም በረሃብ እየገደለ ነው ብላ ታምናለች።
“ከጦርነቱ የተረፉት አሁን ላይ በረሃብ እንዲሞቱ ተፈርዶባቸዋል፤ የአለማቀፉ ፍርድቤት ህልውናቸውን ለማረጋገጥ ትዕዛዝ ማስተላለፍ አለበት” ይላል አዲሱ የደቡብ አፍሪካ አቤቱታ።
እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ፍጅት እየፈጸመች ነው የሚል ክስ ያቀረበችው ፕሪቶሪያ፥ ከቴል አቪቭ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን እስከማቋረጥ መድረሷን ሬውተርስ አስታውሷል።
አለማቀፉ ፍርድቤትም በጥር ወር 2024 እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመው ጥቃት ንጹሃንን ኢላማ ያላደረገና የዘር ፍጅትን ለማስቀረት የወጡ ህጎችን የሚተላለፍ እንዳይሆን ማሳሰቡ አይዘነጋም።
ደቡብ አፍሪካ የአለማቀፉ ፍርድ ቤት በአስቸኳይ የእስራኤልን የራፋህ ዘመቻ እንዲያስቆም ያቀረበችው አቤቱታ ምላሽ ቢያገኝም ተፈጻሚነቱ ግን አጠራጣሪ ነው ይላሉ ተንታኞች።
ደቡብ አፍሪካን “የሃማስ የህግ ክፍል” እያለች የምትወቅሰው ቴል አቪቭ፥ በጋዛ የማካሂደው ጦርነት አለማቀፍ የሰብአዊ ህጎችን የጣሰ አይደለም በሚል ስትከራከር ቆይታለች።
አሜሪካ በበኩሏ ወደ እስራኤል የላኩት የጦር መሳሪያ አለማቀፍ የጦርነት ህጎችን በጣሰ መንገድ ጥቅም ላይ ውለው ሰብአዊ ጥሰቶች ሳይፈጸሙ አልቀረም የሚል ሪፖርትን አውጥታለች።
ዋይትሃውስ በቅርቡም የአሜሪካ ቦምቦች በጋዛ የንጹሃን ፍልስጤማውያንን ህይወት መቅጠፋቸውን ማመኑ የሚታወስ ነው።
በራፋህ ዘመቻ ዙሪያ ከዋሽንግተን ጫናው የበረታባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው፥ “አሜሪካ ጦር መሳሪያ ድጋፍ ካቋረጠች በጥፍራችንም ቢሆን እንዋጋለን እንጂ ወደኋላ አንመለስም” ማለታቸው የሚታወስ ነው።