የአለም ፍርድቤት እስራኤል በፍልስጤም ግዛቶች ላይ ወረራ መፈጸሟ ህገወጥ ነው አለ
አይሲጄ እስራኤል በዌስትባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌም የምታካሂደውን የሰፈራ ፕሮግራም እንድታቆምም አዟል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው ፍርድ ቤቱ “ሀሰተኛ ውሳኔ” ማሳለፉን ተቃውመዋል
የመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ ፍርድ ቤት እስራኤል በፍልስጤም ግዛቶች ላይ የምትፈጽመው ወረራ ከአለማቀፉ ህግ የተቃረነ ነው አለ።
በተለምዶ የአለም ፍርድ ቤት የሚሰኘው የአለማቀፉ የፍትህ ፍርድቤት (አይሲጄ) እስራኤል በዌስትባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌም እንዲሁም በጋዛ ሰርጥ የምታካሂደውን “ህገወጥ” የሰፈራ ፕሮግራም እንድታቆም ብያኔ አስተላልፏል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው ፍርድ ቤቱ “ሀሰተኛ ውሳኔ” አሳልፏል ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
“አይሁዳውያን በራሳቸው መሬት ወራሪ ሊባሉ አይገባም፤ የአለም ፍርድቤት ውሳኔ ታሪካዊውን እውነት የሚያጣምም” ነው ሲሉም ነው የተናገሩት።
የፍልስጤም የነጻነት ድርጅት (ፒኤልኦ) ዋና ጸሃፊ ሁሴን አል ሼክ ግን የፍርድቤቱን ውሳኔ “ታሪካዊ” ብለውታል።
የአለማቀፉ ፍርድቤት ውሳኔ አስገዳጅነት ባይኖረውም ፖለቲካዊ ተጽዕኖው ግን ቀላል እንደማይሆን ይነገራል።
አይሲጄ እስራኤል ለ57 አመታት በተቆጣጠረቻቸው የፍልስጤም ግዛቶች ህጋዊነት ላይ አቋሙን ሲያንጸባርቅ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል።
መቀመጫውን ኔዘርላንድስ ዘ ሄግ ያደረገው ፍርድቤቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ባለፈው አመት ጥያቄ ካቀረበ በኋላ ጉዳዩን ሲመረምር መቆየቱን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።
ፍርድቤቱ እስራኤል በፍልስጤማውያን ዙሪያ በቀረጸቻቸው ፖሊሲዎችና በወረራ በተያዙት የፍልስጤም ግዛቶች ህጋዊነት ዙሪያ አስተያየቱን እንዲሰጥ ነበር የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ የጠየቀው።
የፍርድቤቱን ግኝቶች ያቀረቡት የአይሲጄ ፕሬዝዳንት ናዋፍ ሳላም “እስራኤል በሀይል በተቆጣጠረቻቸው የፍልስጤም ግዛቶች መቆየቷ ህገወጥ ነው” ብለዋል።
“እስራኤል በሃይል ከተቆጣጠረቻቸው የፍልስጤም ግዛቶች በተቻለ ፍጥነት የመውጣት ግዴታ አለባት” ሲሉም ነው የተደመጡት።
እስራኤል በፈረንጆቹ 2005 ከጋዛ ሰርጥ መውጣቷን ብታሳውቅም አሁንም በቁጥጥሯ ስር መሆኑን በመጥቀስም አሁንም ወረራዋ እንዳልቆመ አብራርተዋል።
የተመድ ከፍተኛው ፍርድ ቤት እስራኤል በዌስትባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌም በህገወጥ መንገድ ያሰፈረቻቸውን ዜጎቿን ማስወጣትና በወረራው ምክንያት ለተጎዱ ፍልስጤማውያን ካሳ መክፈል አለባት ብሏል።
እስራኤል በወረራ በያዘቻቸው የፍልስጤም ግዛቶች ውስጥ የሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ “በጎሳና በሃይማኖት ላይ የተመሰረተ ስልታዊ መድልኦ” እንደምትፈጽምም ፍርድቤቱ አመላክቷል።
የፍስጤማውያንን የተፈጥሮ ሃብት ከመበዝበዝ ባሻገር የራሳቸውን እድል የመወሰን መብት ነጥቃለች ያለው ፍርድቤቱ፥ ሀገራት ለእስራኤል የሚያደርጉት ድጋፍ አሁን ያለውን ሁኔታ የሚያስቀጥል በመሆኑ ለቴል አቪቭ ድጋፍ ከማድረግ እንዲቆጠቡ መክሯል።
እስራኤል ከ1967 አንስቶ 700 ሺህ አይሁዳውያን በዌስትባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌም አስፍራለች።
አይሲጄ የሰፈራ ፕሮግራሙን ህገወጥ ነው ቢለውም እስራኤል ግን ከአለማቀፉ ህግ የተቃረነ አይደለም በሚል በተደጋጋሚ ትሞግታለች።