ተመድ ወደ ጋዛ የጦር መሳሪያ እንዲያስገባ እስራኤል ፈቃድ ሰጠች
የጦር መሳሪያው በጋዛ የተበራከተውን ህገወጥነት ለመከላከል ጥቅም ላይ የሚውል ነው ተብሏል
ከዚህ ባለፈ የእርዳታ ጫኝ ተሸርካሪዎች በእስራኤል ድንበር ውስጥ ከሚያጋጥማቸው ጥቃት ለመጠበቅ የጦር መሳሪያዎቹ ወሳኝ መሆናቸው ተገልጿል
ተመድ ወደ ጋዛ የጦር መሳሪያ እንዲያስገባ እስራኤል ፈቃድ ሰጠች።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ወደ ጋዛ የጦር መሳሪያ፣ የታጠቁ ተሸከርካሪዎች እና የመገናኛ ሬድዮዎችን እንዲያስገባ ከእስራኤል ፈቃድ አግኝቷል፡፡
ላለፉት ወራት በእርዳታ መጋዘኖቹ እና በሰራተኞቹ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ያጋጠመው ድርጅቱ በአካባቢው የሚገኝውን ንብረት እና ሰራተኞች ከጥቃት ለመከላከል የጦር መሳሪያ ወደ ጋዛ ለማስገባት ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡
በአሜሪካ ተጽእኖ ጥያቄውን የተቀበለችው እስራኤል የጦር መሳሪያ እና የመገናኛ ሬድዮዎቹን አይነት በቅድሚያ ማወቅ እንደምትፈልግ ገልጻለች፡፡
በጋዛ በሚገኝው ከፍተኛ የምግብ እና መሰረታዊ ሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እጥረት የተነሳ ከስርቆት ጋር በተያያዘ በአካባቢው የሚገኙ የተመድ የእርዳታ መጋዘኖች በተለያየ ጊዜ ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን የእርዳታ ሰራተኞችም በዚሁ ጥቃት ጉዳት አስተናግደዋል፡፡
2.3 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች በሚኖርባት ጋዛ 90 በመቶው ህዝብ ከመኖርያው ተፈናቅሎ በመጠለያዎች ይገኛል፡፡
ተመድ በመጋዘኖቹ ላይ ከሚያጋጥመው ስርቆት ባለፈ ወደ ጋዛ ለመግባት በሚያቋርጣቸው የእስራኤል አካባቢዎች አክራሪ የቀኝ ዘመም ቡድኖች እርዳታ በጫኑ ተሸከርካሪዎች ላይ ጉዳት ከማድረስ ባለፈ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዳይገባ አናሳልፍም ብለው ነበር፡፡
በነዚህ አካባቢዎች ላይ የእርዳታ ጭነት አሽከርካሪዎች እና ሌሎች ሰራተኞች ወደ ጋዛ እንዳያልፉ ከመከልከላቸው ባለፈ ድብደባ እና ጥቃት እንደደረሰባቸውም ተሰምቷል፡፡
ተመድ ፈቃድ ያገኝባቸው የጦር መሳሪያዎች በእስራኤል ድንበር ውስጥ አሽከርካሪዎቹ እራሳቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉ ጥቅም ላይ ይውላሉ ተብሏል፡፡
በጋዛ የሰበአዊ ጉዳዮች ምክትል አስተባባሪ ስኮት አንደርሰን እንደሚሉት በጋዛ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ህግ እና ስርአትን የሚያስከብረው መዋቅር ፈርሷል። በዚህ የተነሳ የእርዳታ ሰራተኞች እና መጋዘኖች በእጅጉ ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው፡፡
አስተባባሪው አንዳንድ የመገናኛ ሬድዮች እና የታጠቁ ተሸከርካሪዎች ከዛሬ ጀምሮ ወደ ጋዛ መግባት ይጀምራሉ ፤ በአካባቢው የሳተላይት ኢንተርኔት አገልግሎት እንዲጀመር እና ተመድ በጠየቃቸው የጦር መሳሪያ አይነቶች ላይ በቅርቡ ውሳኔ ላይ ይደረሳል ብለዋል፡፡
“በአሁኑ ወቅት ወደ ጋዛ በነጻነት የሚጓጓዙት የንግድ ተሸርካሪዎች ናቸው። እነርሱም የታጠቁ ጠባቂዎች ስላሏቸው ማንም ደፍሮ አይጠጋቸውም ስለሆነም እኛም ተመሳሳዩን እናደርጋለን” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ወደ ሰሜናዊ ጋዛ በቀን ከ25 እስከ 70 እርዳታ ጫኝ ተሸከርካሪዎች ይገቡ እንደነበር የተናገሩት አንደርሰን አሁን ላይ ግን ቁጥሩ እጅግ መቀነሱን አንስተው ጋዛ ከመግባታቸው በፊት መንገድ ላይ የሚያጋጥማቸው ክልከላ ተግዳሮት ስለመሆኑ ነው ያስታወቁት ፡፡