እስራኤል የዓለም ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን ትዕዛዝ ውድቅ አደረገች
ፍርድ ቤቱ እስራኤል በጋዛ ያሉ ሁኔታዎችን የሚያሻሽል እርምጃ እንድትወስድ ካዘዛት ወዲህ በፍልስጤም ጋዛ ያሉ ሁኔታዎች እየተባባሱ ነው ብለዋል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እስራኤል በጋዛ የዘር ማጥፋት ፈጽማለች የሚለውን የደቡብ አፍሪካ ክስ ውድቅ አድርጎታል
እስራኤል፣ አለምአቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት(አይሲጄ) በጋዛዋ የራፋ ከተማ የጀመረችውን ጥቃት እንድታቆም በትናንትናው እለት ያስተላለፈውን ትዕዛዝ እንደማትቀበለው ገልጻለች።
የአይሲጄ ውሳኔ እስራኤል በጋዛ እያካሄደችው ባለው ጦርነት እየደረሱባት ካሉት ተከታታይ ጫናዎች እና አለምአቀፍ መገለል ካደረሱባት እርምጃዎች የቅርብ ጊዜው ነው።
የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ያነበቡት የፍርድ ቤቱ ፕሬዝደንት ንዋፍ ሳሌም እስራኤል በጋዛ ያሉ ሁኔታዎችን የሚያሻሽል እርምጃ እንድትወስድ ፍርድ ቤቱ ካዘዛት ወዲህ በፍልስጤም ጋዛ ያሉ ሁኔታዎች እየተባባሱ ነው ብለዋል።
"የእስራኤል መንግስት በራፋ የሚያካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻ በአስቸኳይ ማቆም እና በፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ላይ ውድመት ሊያስከትል የሚችልን ጥቃት ጨምሮ ማንኛውንም እርምጃ ከመውሰድ መቆጠብ አለባት" ብለዋል ሳሌም።
በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ እስራኤል በግብጽ እና በጋዛ መካከል ያለውን የራፋ ማቋረጫ በመክፈት ሰብአዊ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ እንድታደርግ አዟታል።
እስራኤል መርማሪዎች ወደተከበበችው ጋዛ እንዲገቡ እንድትፈቅድ እና ሁኔታዎችን በአንድ ወር ተመልሰው ሪፖርት እንዲያደርጉም ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ከመላው አለም የተሰባሰቡ 15 አባላት ያሉት የዳኞች ቡድን ትዕዛዙን በሁለት ተቃውሞ በ13 ድጋፍ አጽድቆታል። ከእስራኤል እና ከኡጋንዳ የመጡ ዳኞች ትዕዛዙን ተቃውመውታል።
ውሳኔው የተላለፈው በእስራኤል ላይ የዘርማጥፋት ክስ የመሰረተችው ደቡብ አፍሪካ ከጠየቀች ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው።
አይሲጄ በሁለት መንግስት መካከል የሚኖርን አለመግባባት የሚፈታ የተመድ አካል ነው።
ፍረድ ቤቱ የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች የመጨረሻ እና አስገዳጅ ቢሆንም ከዚህ በፊት ችላ ሲባሉ ቆይተዋል። ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ተግባራዊ የሚያደርግበት አሰራር የለውም።
በጋዛ እያደረገችው ያለውን ዘመቻ ራስን የመከላከል እርምጃ ነው የምትለው እስራኤል የሚቀርብባትን የዘርማጥፋት ክስ አትቀበለውም።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽ/ቤት እስራኤል በጋዛ የዘር ማጥፋት ፈጽማለች የሚለውን የደቡብ አፍሪካ ክስ "ሀሰተኛ፣ አናዳጅ እና የሞራል ተቀባይነት የሌለው" ሲል ውድቅ አድርጎታል።
ጽ/ቤቱ በመግለጫው "እስራኤል አለምአቀፍ ህጎችን እና እሴቶቿን ባከበረ መልኩ ግዛቷን እና ዜጎቿን እየተከላከለች ነው" ብሏል።
አለምአቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) አቃቤ ህግ በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ፣ በመከላከያ ሚኒስትሩ ዩአብ ጋላንት እና በሶስት የሀማስ አመራሮች ላይ የእስር ማዘዣ እንዲወጣባቸው ጠይቋል።
እስራኤል ጥያቄውን የጸረ-ጽዮናዊነት ማሳያ ነው በማለት በጽኑ ተቃውማዋለች።
እስራኤል፣ ሀማስ በፈጸመው ጥቃት 253 ማገቱን እና 1200 ሰዎችን መግደሉን ተከትሎ በጋዛ እያካሄደችው ባለው ጥቃት ከ35ሺ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ባለስጣን ገልጸዋል።