"የምመረጥ ከሆነ ብሔራዊ ሊግን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ የሊግ ውድድሮች የቴሌቪዥን ስርጭ እንዲያገኙ አደርጋለሁ" - አቶ ኢሳያስ ጅራ
የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ ቦታ የጉባኤውን ደህንነት ለመጠበቅ በማሰብ ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ መምጣቱን ተናግረዋል
ከሊግ ካምፓኒው ጋር በመተባበር "ክለብ ላይሰንሲንግ" ላይ እንደሚሰሩ አቶ ኢሳያስ አስታወቁ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ሆነው በድጋሚ የሚመረጡ ከሆነ "ብሔራዊ ሊግን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ የሊግ ውድድሮች የቴሌቪዥን ስርጭት እንዲያገኙ" እንደሚያደርጉ ተናገሩ፡፡
እግር ኳስ ፌዴሬሽኑን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት ከቀረቡ ሶስት እጩዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ኢሳያስ እጩነታቸውንና ቢመረጡ ሊሰሩ የሚችሏቸውን ተግባራት በተመለከተ ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ/ም ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫው በባለፉት አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑ ዋና መስሪያ ቤት እንዲኖረው ከማድረግ ጀምሮ የሊግ ካምፓኒ እንዲቋቋም፣ በሁለቱም ጾታ ያለው የብሔራዊ ቡድን ተሳትፎ እንዲያድግና ብሔራዊ ቡድኑ (ዋሊያዎቹ) ከ8 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ እንዲመለሱ ማድረግ ችለናል ብለዋል፡፡
ለክልል ፌዴሬሽኖች እስከ 12 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ድጋፍን ስናደርግ ነበር ያሉም ሲሆን ለዓመታት ግንባታው ተጓቶ የነበረውን የካፍ አካዳሚን ወደ ስራ ለማስገባት፣ ከካፍ እና ከፊፋ ጋር በመነጋገር የአሰልጣኞች ስልጠናዎችን ለማመቻቸት መቻሉን ገልጸዋል፡፡
አቶ ኢሳያስ ፕሬዝዳንት ሆነው በድጋሚ ቢመረጡ የፌዴሬሽኑን ተቋማዊ አደረጃጀት ከማጠናከር በዘለለ፣ ከሊግ ካምፓኒው ጋር በመተባበር "ክለብ ላይሰንሲንግ" ላይ ለመስራት፣ ተጨማሪ የልምምድ ስፍራዎችን ለመገንባት፣ የአሰልጣኞችን አቅም ለመገንባት የሚያስችሉ ስልጠናዎችን ለመስጠት ማቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ ላይ ከመስራት እና ለክልል ፌዴሬሽኖች የተሻለ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር የሙያ ማህበራትን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
ብሔራዊ ሊግ እና ሱፐር ሊግን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ ውድድሮች የቴሌቪዥን ስርጭት እንዲኖራቸው ለማድረግ እሰራለሁም ነው አቶ ኢሳያስ ያሉት፡፡ ለዚህ የሚሆንና ለቀጣዮቹ 4 ዓመታት የሚያገለግል "ሌጋሲ ዶክመንት" አዘጋጅተናልም ብለዋል፡፡
የተጫዋቾች ዝውውር መነሻውን ከ2 ዓመት ከፍ በማድረግና ጣራውን እስከ 5 ዓመት በማድረግ የተረጋጋ የኮንትራት ይዞታን ለመፍጠር እንደሚሰሩም ነው የተናገሩት፡፡
የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ ለምን በድንገት ከጎንደር ሊቀየር እንደቻለ በጋዜጠኞች የተጠየቁት አቶ ኢሳያስ ምርጫውን የማስተዳደር ስልጣን የፌዴሬሽኑ እንደሆነ በመጠቆም የጉባኤውን ደህንነት መጠበቅ ስላለብን ጉባኤውን ወደ አዲስ አበባ አምጥተነዋል ብለዋል፡፡
ጎንደር በጥሩ የደህንነት ይዞታ ላይ ባለበት ሁኔታ በምን ዐይነት የደህንነት ስጋት የጉባኤው ቦታ ሊቀየር እንደቻለና ውሳኔው ሊያሳድር ስለሚችለው አሉታዊ ተጽዕኖዎች ለቀረበላቸው ጥያቄም "እኛ በምንመራውና በምናስተዳድረው እዚህ ቦታ አድርግ ልንባል አንችልም" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
"እየደወለ በአካል ሄጄ ምርጫውን እበጠብጣለሁ የሚል አካል ባለበት ሁኔታ" በተባለው ቦታ ልናካሂድ አንችልም ብለዋል ጉዳዩን ፖለቲካዊ መልክ መስጠት እንደማያስፈልግ በመጠቆም፡፡
ከአሁን ቀደም በጦርነቱ የተቀዛቀዘውን ሁኔታ ለማነቃቃት በሚል ጎንደር ላይ ከ20 ዓመት በታች ውድድር ማድረጋቸውን በማሳያነት በማንሳትም የጉባዔው ቦታ መቀየሩ ከተጠቀሰው ውጭ የተለየ ምክንያት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡
ፌዴሬሽኑን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት ከቀረቡት እጩዎች አንዱ የሆኑት አቶ መላኩ ፋንታ ባሳለፍነው ሰኞ በሰጡት መግለጫ የጉባኤው ቦታ መቀየር ምናልባትም "የተለመደውን የምርጫ አካሄድ ለመድገም በማሰብ የተደረገ" ሊሆን እንደሚችል መናገራቸው ይታወሳል፡፡