ፖለቲካ
ብልጽግና በምርጫው ካሸነፈ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመንግስት መዋቅር ውስጥ ውክልና እንዲኖራው ያደርጋል-ጠ/ሚ ዐቢይ
በምርጫው እለት ዜጎች በነቂስ ወጥተው ድምፅ በመስጠታቸውም አመስግነዋል
ኢትዮጵያውያን ከፖለቲካ ይልቅ ሀገር ትቀድማለች የሚል መርሕ ኢትዮጵያን አሸናፊ አድርገዋታል ብለዋል
ብልፅግና ፓርቲ በምርጫው የሚያሸንፍ ከሆነ በምርጫው የተፎካከሩ ፓርቲዎችን በየደረጃው ባለው የመንግስት መዋቅር የሚያሳትፍ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ።
የሲቪክ ማህበራት ደርጅቶች ምክር ቤት በዘንድሮው ምርጫ ለተፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምስጋና መርሃ ግብር አካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መርሃ ግብሩን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላፉት መልእክት፤ “ኢትዮጵያ ዘንድሮ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ የቻለችው ሁላችንም ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ በመሥራታችን ነው” ብለዋል።
“ኢትዮጵያውያን ከፖለቲካ ይልቅ ሀገር ትቀድማለች የሚል መርሕ አንገበው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ ሀገራቸውን አሸናፊ አድርገዋታል” ብለዋል ።
በምርጫው ፓርቲያቸው ብልጽግና አሸናፊ ከሆነ ተፎካካሪ የነበሩ ፓርቲዎችን ከታች ጀምሮ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሳትፋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የምርጫ ውጤቱ በተቃራኒ ሆኖ ብልጽግና ፓርቲ የሚሸነፍ ከሆነም የኢትዮጵያን አሸናፊነት ለማረጋገጥ መንግስት ለአሸናፊው የፖለቲካ ፓርቲ ስልጣኑን በሰላማዊ መንገድ እንደሚያስረክብም ተናግረዋል፡፡