ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሰራዊቱ ከትግራይ ክልል ስለመውጣቱ ምን አሉ?
ከትግራይ ክልል የወጣነው ለህዝቡ ለ15 ቀናት አሊያም ለ1 ወር የጥሞና ጊዜ እንስጥ ብለን ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትግራይ ክልል “መያዝ ያለብንን እና መቆየት ያለብን ቦታዎችን እንይዛለን” ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ሰራዊቱ ከትግራይ ክልል እንዲወጣ የተደረገው አሁን ላይ ህወሓት ለሀገር አስጊ ባለመሆኑ እና ኢትዮጵያ ካሉባት ችግሮች ውስጥ ቅድሚያ የምትሰጠው ሌላ ጉዳይ በመኖሩ” ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ጉዳይ በተመለከተ ትናንት ምሽት ለጋዜጠኞች ገለጻ ባደረጉበት ወቅት ነበር።
“መቀሌ ከስምንት ወራት በፊት የነበራት የስበት ማእከልነት እና የማይታወቅ ሀብት ማእከልነትን አሁን ላይ አጥታለች፤ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ልክ እንደ ሌሎች ከተሞች ሆናለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ለዚህ ነው ከተማዋን ለቀን የወጣነው” ሲሉም ተናግረዋል።
“የህወሓት ዓላማ እናሸንፍ እና መንግስት እንሁን አይደለም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ወድቂያለሁ እና አብረን ተያይዘን እንውደቅ የሚል ስትራቴጂ ነው የሚከተለው” ብለዋል።
“መንግስት እዛ የመቆየት ፍላጎት የለውም፤ ሌላ የሚያሰጋው ሀይል ስላለ የሚመታውን መትቶ፤ መሳሪያውን ወስዶ ወጥቷል ሲሉም ተናግረዋል።
“መጀመሪያ እንደ ወታደር ዩኒፎርም የለበሰ፣ የሚቆምበትን ቦታ የሚያውቅ መሳሪያ የታጠቀ ሀይል ነበር የገጠመን፤ እሱን በ15 ቀን ጨረስን፣ ቀጥሎ በሽፍታነት መልክ የተደበቀ ቡድን ነው ገጠመን እሱንም ማፈላለግ እና መደምሰስ ተችሎ ነበረ፣ አሁን ላይ ግን ውጊያው ተቀይሯል፤ ወታደሩን ከጀርባው በኩል በመውረር በክላሽ እና በገጀራ ማጥቃት ነው የተካሄደው” ብለዋል።
“መቐለ ላይ ወደ አራት ክፍለ ጦር የሚጠጋ ሰራዊት ነበረ፤ ነገር ግን ሁሉንም እንደ ጠላት የማየት አዝማሚያ ስለመጣ በታሪክ ውስጥ ጥቁር ጠባሳ ከሚፈጠር በሚል ሰራዊቱ እንዲወጣ የተደረገው” ሲሉም ተናግረዋል።
“ሰራዊቱ እንዲወጣ የተደረገው የጥሞና ጊዜ ለህዝቡ ያስፈልገዋል በሚል ነው፤ ከ15 ቀን አሊያም አ1 ወር በኋላ ውጤቱን እናያለን” ሲሉም ተናረዋል።
“ሆኖም ግን መያዝ ያለብንን እና መቆት ያለብን ቦታዎች ላይ ይዘን እንቆያለን” ያሉ ሲሆን፤ “ባለንበት ሊገጥመን የሚመጣ የተደራጀ ሀይል ካለም ለማስተናገድ ዝግጁ ነን” ብለዋል።
መንግስት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቀረበለትን ጥያቄ መሰረት በማድረግ የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁን ባለፈው ሰኞ እለት ነበር ያስታወቀው፡፡ የመንግስትን የተኩስ አቁም ውሳኔ ተመድ፣አሜሪካና የአፍሪካ ህብረት የመንግስትን ውሳኔ በአዎንታ እንደሚያዩት ገልጸዋል።