“የዜጎችን ግድያ ማስቆም ካልተቻለ ለምን አንበተንም?” የፓርላማ አባላት
“ኦነግ ሸኔ፣ ሕወሓትና የቤንሻንጉል ጉምዝ ነፃ አውጪ ግንባር”ን በተመለከተም ሀሳቦች ተነስተዋል
በንጹሃን ጭፍጨፋ ዙሪያ ም/ቤቱ ውሳኔ እንዲያሳልፍ የሚያስችል የውሳኔ ሀሳብ 2 ቋሚ ኮሚቴዎች እንዲያዘጋጁ ታዟል
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ በነበረው ስብሰባ ላይ ከአባላት “በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተለይም በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል እየተፈጸሙ ያሉ ግድያዎችን ማስቆም ካልተቻለ ምክር ቤቱ መበተን ነው ያለበት” የሚል ሀሳብ መነሳቱን ስብሰባውን የተከታተሉ አባል ገለጹ፡፡
ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉት እኚህ የምክር ቤት አባል ለአል ዐይን እንደገለጹት ምክር ቤቱ ዛሬ ሌሎች አጀንዳዎች ቢኖሩበትም “በሀገሪቱ በንጹሃን ላይ እየደረሱ ያሉ ግድያዎችን ዋነኛ አጀንዳ እንዲሆን አድርጓል” ብለዋል፡፡ ለመገናኛ ብዙሃን ዝግ በነበረው በዚህ ስብሰባ የምክር ቤት አባላት ረጅም ሰዓት ወስደው የተወያዩት የንጹሃን ጭፍጨፋን በተመለከተ ምን መደረግ አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ስለመሆኑም ምንጫችን ገልጸዋል፡፡ የዛሬው ስብሰባ የተጀመረው በህሊና ጸሎት ቢሆንም አባላቱ ”ሁል ጊዜ ሰቆቃ መስማትና የህሊና ጸሎት ማድረግ ሰልችቶናል” ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
የም/ቤት አባላቱ “ኦነግ ሸኔ፣ ሕወሓትና የቤንሻንጉል ጉምዝ ነፃ አውጪ ግንባር የተባሉ ድርጅቶች በአሸባሪነት ለምን እንደማይፈረጁም” ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ይህ ጥያቄ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ጋር እንደደረሰም ነው ምንጫችን ያስታወቁት፡፡ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ዛሬ በምክር ቤት ለሌላ ጉዳይ ቢገኙም በዚህ ጉዳይ ግን ዕድል ተሰጥቷቸው አስተያየት አለመስጠታቸው ተሰምቷል፡፡
ታህሳስ 27 ቀን 2013 ዓ.ም በምክር ቤት ተገኝተው ከአባላት የቃል ጥያቄ እንደሚቀርብላቸው የሚጠበቁት ዶ/ር ጌዲዮን ያኔ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንደሚሰጡ ይጠበቃል ነው የተባለው፡፡
ሌላውና በአባላቱ በከፍተኛ ሁኔታ የተነሳው ጉዳይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በንጹሃን ጭፍጨፋ ዙሪያ ምን ማድረግ አለበት በሚለው ነው፡፡ በዚህ ጉዳይየተለያዩ ሀሳቦች የተነሱ ሲሆን ከአስፈጻሚ አካላት ሪፖርት እንዲያቀርቡ ይደረግ ወይስ የቃል ጥያቄ ይቅረብላቸው የሚሉ ሃሳቦች ቀርበዋል፡፡
በመጨረሻም የሕግ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና ውጭ ግንኑነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክር ቤቱ ምን ማድረግ እንዳለበት የውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርቡ በድምጽ ብልጫ ተወስኗል ነው የተባለው፡፡
በዚህም መሰረት ሁለቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ፣ ምክር ቤቱ በንጹሃን ጭፍጨፋ ዙሪያ ምን ውሳኔ ማስተላለፍ እንዳለበት የውሳኔ-ሀሳብ እንዲያዘጋጁና በሚቀጥለው የምክር ቤቱ ስብሰባ ይዘው እንዲቀርቡ ተወስኗል፡፡