“ጥቃት ፈጻሚዎች ከታወቁ ፣ ለምን የማያዳግም እርምጃ መውሰድ አልተቻለም?” የም/ቤት አባላት
በም/ኦሮሚያ በተፈጸመው ግድያ ጠ/ሚ ዐቢይ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቋል
“ከ2 ዓመት በፊት በለውጥ ስሜት ስራ ስንጀምር የነበረን ተስፋ አሁን የለም” ብለዋል የም/ቤት አባላቱ
“ጥቃት ፈጻሚ የተባሉት ከታወቁ ፣ ለምን የማያዳግም እርምጃ መውሰድ አልተቻለም?” የህዝብ ተወካዮች ም/ ቤት አባላት
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ዛሬ ሲካሄድ አፈጉባዔ ታገሰ ጫፎ ለዕለቱ የተያዙ አጀንዳዎችን ይፋ ቢያደርጉም አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ዜጎች ማንነታቸውን መሰረት ባደረገ ጥቃት እየተጨፈጨፉ ሌላ አጀንዳ ላይ አንወያይም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
በዚህም መሰረት አባላቱ ከ2 ሰዓት በላይ ስለዚሁ ጉዳይ እንባ እየተናነቃቸው ጭምር ሀሳባቸውን በስሜት መግለጻቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
“በመግለጫ መፍትሄ አይመጣም ፤ ድርጊትና እርምጃ ያስፈልጋል ፤ ዛሬ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እየተጨፈጨፉ ዝም ካልን ነገ በሺዎች የሚቆጠሩ እንዲጨፈጨፉ መፍቀድ ነው” ሲሉም መሞገታቸው ተሰምቷል፡፡
አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ የዕለቱን አጀንዳዎች በዝርዝር ከማቅረባቸው በፊት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ከትናንት በስቲያ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓም በዜጎች ላይ የደረሰውን ጭፍጨፋ በተመለከተ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ የሚያሳስብ መግለጫ ማንበባቸውም ተጠቅሷል፡፡
የህሊና ፀሎት ከተደረገ በኋላ ወደ ዕለቱ አጀንዳዎች ለመገንባት ማስተዋወቅ ሲጀምሩ፣ የተለያዩ የምክር ቤቱ አባላት እዚህም እዚያም እጅ እያወጡ ተራ ሳይጠብቁ መናገር የጀመሩ ሲሆን “በዜጎች ላይ የብሔር ማንነትንና ሃይማኖትን መሰረት ባደረገ ጥቃት በየጊዜው እየተጨፈጨፉ በምን ሞራል ነው ሌላ አጀንዳ ላይ የምንነጋገረው? “ሲሉ መጠየቃቸውንም የምክር ቤት ምንጮች ጠቅሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ብሔራዊ የመረጃ ደህንነት አገልግሎት ፣ የሰላም ሚኒስቴር ፣ የመከላከያ ሚኒስቴር እና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት መጥተው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያና ምላሽ እንዲሰጡም ተጠይቋል፡፡
“አልሸባብና አይ ኤስ ኤስን ለመመከት በሰው ሀገር ጭምር ሰላም የሚያስከብረው የመከላከያ ሰራዊታችን ፣ ዕውን ኦነግ ሸኔን ማሸነፍ አቅቶት ነው ወይ” ሲሉ ስሜታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው እያነቡ የተናገሩት ብርቱካን ሰብስቤ የተባሉ የሕ/ተ/ም/ቤት አባል ጥያቄ አንስተዋል፡፡
“ከ2 ዓመት በፊት በለውጥ ስሜት ስራ ስንጀምር የነበረን ተስፋና ሞራል አሁን የለም“ብለዋል አባላቱ፡፡
አባላቱ የምዕራብ ወለጋ አካባቢ የሰላም የማጣት ችግር እንዳለበት እየታወቀ የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ከሚችል ሌላ አካል ጋር ርክክብ ሳይደረግ መከላከያ ሰራዊት ለምን ከዛ ስፍራ ለቆ እንደወጣ መጠናትና ሪፖርት ማቅረብ እንደሚያስፈልግ በመጥቀስ ከአስፈፃሚ የመንግስት አካላትም ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
አማራን እየለዩ ማጥቃት አሁን የተጀመረ ሳይሆን፣ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ ገልጸዋል፡፡ ከአማራ ክልል ውጭ በሚኖሩ አማራዎች ላይ ተመሳሳይ ግድያ እና የጅምላ ጭፍጨፋ ሲካሄድ መቆየቱን ያስታወሱት ምክትል አፈጉባዔዋ፣ ችግሩ ከሕገ-መንግስቱ የመነጨ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
“የሰላም ሚኒስቴር ባለበት ሀገር የሰው ልጅ እንደቅጠል እየረገፈ ማየት እጅግ ያማል“ ያሉት ምክትል አፈ-ጉባዔዋ፤ “የሕዝብን ደኀንነት ማስጠበቅ የማንችል ከሆነ የእኛ መኖር ትርጉም አልባ ስለሚሆን የዜጎች መፈናቀል እና ግድያ መቆም አለበት“ ሲሉ አሳስበዋል፡፡
መንግስት ጥቃት በተፈፀመ ቁጥር፣ ጥቃት አድራሾቹን እየገለጸ መምጣቱን ያነሱት አባላቱ “ጥቃት ፈጻሚ የተባለው ከታወቀ ፣ ለምን የማያዳግም እርምጃ መውሰድ አልተቻለም?“ ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
በዛሬው መደበኛ ስብሰባ ሕወሃት እና ኦነግ ሸኔ በምክር ቤቱ በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ የጠየቁ የምክር ቤት አባላትም ነበሩ፡፡
በአጠረ ጊዜ ውስጥ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት በምክር ቤቱ ተጠርተው ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡና አስፈላጊው ውሳኔ እንዲተላለፍም ተወስኗል፡፡