ዶ/ር ወርቅነህ በቀጣይ በሱዳን የሚመሰረተውን ሁሉን አቀፍ መንግስት ለማገዝ ኢጋድ ዝግጁ እንደሆነም ገልጸዋል
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት/ኢጋድ/ በዛሬው እለት በሱዳን ስልጣን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመመለስ የተደረገውን ስምምነት አደነቀ።
በዛሬው እለት በካርቱም በሚገኘው ቤተ መንግስት የተደረገው የፖለቲካ ስምምነት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ኃምዶክን ጨምሮ የሲቪል አስተዳዳሩ ወደ ቦታው እንዲመለሱና መፈንቅለ መንግሰቱን ተከትሎ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ የሚያስችል ነው ተብሎለታል።
ይህንን ተከትሎም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት/ኢጋድ/ ዋና ጸሃፊ ደ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ሱዳናውያንን “እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል።
የሀገሪቱ አንድነት ለማጠናከርና ስምምነቱ እውን እንዲሆን የበኩላቸውን ኃለፊነት የተወጡት ሁሉም አካላትምን ማመስገናቸውንም አል ዐይን ከኢጋድ ያገኘው መግለጫ አስታውቋል።
ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ “በስምምነቱ መሰረት በቀጣይ በሱዳን የሚመሰረተውን ሁሉን አቀፍ መንግስት ለማገዝና ለስምምነቱ ተግባራዊነት ኢጋድ ዝግጁ ነው” ብለዋል።
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በሱዳን የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት ማውገዙ የሚታወስ ነው።
በሱዳን በሃገሪቱ ጦር ዋና አዛዥ ጀነራል አብዱል ፋታህ አልቡርሃን የሚመራ አዲስ ወታደራዊ መንግስት መመስረቱ የሚታወስ ነው።
ይህንን ተከትሎም በወታደሩ ተግባር የተበሳጩ ሱዳናውያን በካርቱም እና በሌሎችም የሀገሪቱ ጎዳናዎች ላይ በመውጣት ቁጣቸውን ሲገልጹ ነበረ ሲሆን፤ በተቃውሞ ሰልፎቹ ላይ በሱዳን ጦር የተገደሉ ሰላማዊ ሰልፈኞች ቁጥር 40 ደርሷል።
ተመድን ጨምሮም በርካታ ሀገራት ወታደራዊ አመራሩ ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳድር እንዲመልስ ድርድር እንዲጀመር ሲወተውቱ መቆየታቸውም አይዘነጋም።