የሰጠመችው የብሪታንያ መርከብ በባህር ብዝሃህይወት ላይ ምን ተጽዕኖ ይኖራታል?
በሃውቲዎች ተመታ የሰጠመችው መርከብ 21 ሺህ ሜትሪክ ቶን አሞኒየም ፎስፌት እና ነዳጅ ጭና እንደነበር ተጠቅሷል
ኢጋድ የመርከቧ መስመጥ ኑሯቸው በአሳ ማስገር ለተመሰረተ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች አደገኛ ነው ብሏል
153ኛ ቀኑን የያዘው የጋዛ ጦርነት የቀይ ባህር ደህንነትን አሳሳቢ ካደረገው ወራት ተቆጥረዋል።
የአለማችን ከ10 በመቶ በላይ ሸቀጥ የሚመላለስበት የንግድ መስመር ቀይ ባህር የየመን ሃውቲ ታጣቂዎች በየቀኑ ሚሳኤል የሚወረውሩበት ሆኗል።
አሜሪካና አጋሮቿ የቡድኑን ጥቃት ለማስቆም በየመን የሚፈጽሙት ድብደባም ውጥረቱን ከመቀነስ ይልቅ ይበልጥ እያባባሰው ነው።
የቀይ ባህር ደህንነት ችግር ውስጥ መውደቅ ለጉዞ ተመራጭ ለሚያደርጉት መርከቦች ብቻ ሳይሆን በባህር ውስጥ ለሚኖሩ ነፍሳትም ስጋት ከፈጠረ ቆይቷል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በሚሳኤል ተመትታ በየመኗ ሆዴይዳህ ወደብ አቅራቢያ ከአምስት ቀናት በፊት የሰጠመችው መርከብም ከባድ የብዝሃ ህይወት አደጋ ደቅናለች።
“ሩብይማር” የሚል ስያሜ ያላት መርከብ 21 ሺህ ሜትሪክ ቶን አሞኒየም ፎስፌት ማዳበሪያ እና ነዳጅ ጭና ነበር ተብሏል።
የየመን ባለስልጣናት መርከቧ ከመስጠሟ አስቀድሞ መርከቧ የጫነችው ማዳበሪያ እና ነዳጅ ወደ ባህር ውስጥ ሲገባ አሳዎችን ጨምሮ በውሃ ውስጥ የሚኖሩ ነፍሳትን ህይወት አደጋ ላይ ይጥላል ሲሉ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ኢጋድ በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫም የሩብይማር መርከብ መስመጥ በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረሰላጤ ከፍተኛ አደጋ ደቅኗል ብሏል።
መርከቧ የጫነችው ማዳበሪያ ኬሚካሎች ከውሃ ጋር ሲቀላቀሉ የሚፈጠረውን ብክለትና የብዝሃ ህይወት ቀውስ ለመፍታት እስከ 30 አመታት ሊወስድ እንደሚችል በመጥቀስም በአፋጣኝ መፍትሄ እንዲፈለግ ጠይቋል።
የመርከቧ መስጠም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አሳ በማስገር ህይወታቸውን የሚመሩ አፍሪካውያንን ህይወት ችግር ውስጥ የሚከት መሆኑንም በማከል።
ኢጋድ በቀይ ባህር በሚጓዙ መርከቦች ላይ የሚቃጣ ጥቃት እንዲቆምና ውጥረቱን የሚያረግብ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግም ጠይቋል።
ክፍለ አህጉራዊ ድርጅቱ ስራ የሚበዛበትን የንግድ መስመርና የባህር ውስጥ ስነምህዳር ለማስጠበቅ አዲስ እቅድ በማውጣት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።