በሃውቲ የሚሳኤል ጥቃት የሶስት መርከበኞች ህይወት አለፈ
በላይቤሪያ የተመዘገበችውና በግሪክ ኩባንያ የምትተዳደረው መርከብ በእሳት መያይዟ እና ከአራት በላይ መርከበኞችም መቁሰላቸው ተገልጿል
በሚሳኤል የተመታችው መርከብ ውስጥ 23 የፊሊፒንስ፣ ቬትናም፣ ሲሪላንካ፣ ህንድ እና ኔፓል ዜግነት ያላቸው ሰራተኞች ነበሯት ተብሏል
የየመኑ ሃውቲ ታጣቂ ቡድን ባደረሰው የሚሳኤል ጥቃት ሶስት መርከበኞች ተገደሉ።
ከየመን ኤደን ወደብ በ92 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ሃውቲ ሃላፊነቱን እንደሚወስድ ገልጿል።
በሚሳኤል የተመታች መርከብ “ ትሩ ኮንፊደንስ” የባርባዶስ ሰንደቅ አላማ የምታውለበልብ ሲሆን፥ በላይቤሪያ የተመዘገበችና በግሪክ ኩባንያ የምትተዳደር ናት።
በመካከለኛው ምስራቅ የሚንቀሳቀሰው የአሜሪካ ማዕከላዊ እዝ በሚሳኤል ጥቃቱ መርከቧ ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዷንና አራት መርከበኞችም ክፉኛ መቁሰላቸውን መግለጹን ሬውተርስ ዘግቧል።
መርከቧን የሚያስተዳድረው የግሪክ ኩባንያ “ሰርድ ጃኑዋሪ ማሪታይም” መርከቧ በእሳት መያያዟንና ቀሪዎቹ የመርከቧ ሰራተኞች አሁን ላይ ያሉበት ሁኔታ አለመታወቁን ገልጿል።
በሚሳኤል የተመታችው መርከብ ውስጥ 23 የፊሊፒንስ፣ ቬትናም፣ ሲሪላንካ፣ ህንድ እና ኔፓል ዜግነት ያላቸው ሰራተኞች እንደነበሩም ነው ያስታወቀው።
የፊሊፒንስ መንግስት በሚሳኤል ጥቃቱ ከሞቱት ሶስት መርከበኞች መካከል ሁለቱ ፊሊፒናውያን መሆናቸውንና ሁለት ዜጎቹም መቁሰላቸውን ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
የብሪታንያ ማሪታይም ንግድ ድርጅት ሁሉንም ሰራተኞች በሚሳኤል ከተመታችው መርከብ ማስወጣት መቻሉን ነው የገለጸው።
ከሁለት ሳምንት በፊት በሃውቲዎች ጥቃት የተፈጸመባት የብሪታንያ እቃ ጫኝ መርከብ “ሩብይማር” ከአምስት ቀናት በፊት መስጠሟ መገለጹ የሚታወስ ነው።
እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የምታደርሰውን ድብደባ ካላቆመች በቀይ ባህር በሚጓዙ የእስራኤል፣ የብሪታንያ እና አሜሪካ መርከቦች ላይ ጥቃቴን እቀጥላለሁ ያለው ሃውቲ በሰዎች ህይወት ላይ ጉዳት ያደረሰ የሚሳኤል ጥቃት ሲፈጽም የትናንቱ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
መርከበኞቿ የተገደሉባት “ትሩ ኮንፊደንስ” ባለቤት እና አስተዳዳሪው የግሪክ ኩባንያ በጋራ ባወጡት መግለጫ መርከቧ ከአሜሪካ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የላትም ብለዋል።
የሃውቲ ጥቃት አሜሪካ እና ብሪታንያ በየመን የቡድኑ ይዞታዎች ላይ የሚፈጽሙትን የአየር ድብደባ እንዲያጠናክሩ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ተገምቷል።